የተከለከሉ ግለሰቦችን በገንዘብ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባትና በማስወጣት ሂደት የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ጊዜ ቀጠሮ ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተከለከሉ ግለሰቦችን በገንዘብ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባትና በማስወጣት ሂደት እንዲሁም በፓስፖርት ድለላ ተግባር የተጠረጠሩ 10 ግለሰቦች ላይ ጊዜ ቀጠሮ ተሰጠ።
በሕገወጥ መንገድ ከ20 ሺህ እስከ 7 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ጉቦ በመቀበል ሰነድ አልባ ሰዎችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡና ከሀገር እንዲወጡ በማድረግ ሂደት እንዲሁም ከሕገወጥ የፓስፖርት አሰጣጥ ሂደት ጋር ተያይዞ የተጠረጠሩ ደላሎችና የውጭ ሀገር ዜጎችን ጨምሮ 10 ግለሰቦች ለ2ኛ ጊዜ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው ታይቷል።
በነ አለሚቱ የኔአየው ዳኛቸው በሚል መዝገብ ከተካተቱ 10 ተጠርጣሪዎች መካከል ሁለት ደላሎች፣ ሁለት የውጭ ሀገር ዜጎች ቀሪዎቹ የኤርፖርት እና የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ሰራተኞች ይገኙበታል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዘርፍ መርማሪ በተጠርጣሪዎች ላይ ከዚህ በፊት በተሰጠው ጊዜ ቀጠሮ የ8 ተጠርጣሪዎችን ቃልና የ18 ምስክሮችን ቃል መቀበሉን፣ ተጠርጣዎችን የጣት አሻራ ማስነሳቱንና በቤታቸው በብርበራ ያገኘውን ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ለምርመራ መላኩን፣ የኦዲት ሪፖርት ውጤት እንዲሰጠው መጠየቁን፣ ለባንኮችና ለተቋማት ማስረጃ እንዲሰጠው መጠየቁን እንዲሁም የስራ መዘርዝራቸውን ከሚሰሩበት ተቋም ማምጣቱን ገልጿል።
ቀረኝ ካላቸው ስራዎች መካከል የተጨማሪ ምስክር ቃል መቀበል፣ ከጥቆማዎች ላይ ማስረጃ ማሰባሰብ፣ ከአ/አ ውጪ ባሉ ቅርጫፎች ማስረጃ ማሰባሰብ፣ የኦዲትና የባንክ ማስረጃዎችን ማሰባሰብ እንዲሁም የተጠርጣሪዎችን ሀብት መጠን ማጣራትና ማሳገድ ይገኙበታል።
ከወንጀሉ ውስብስብነት አንጻር ጊዜ እንደሚያስፈልገው የገለጸው መርማሪ ፖሊስ፤ የቀሩ ስራዎችን ለማከናወን የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው÷”በደንበኞቻቸው ላይ ፖሊስ ያቀረበው የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ምክንያቶች ደንበኞቻችንን ተጨማሪ በእስር ሊያቆይ የሚችል አደለም” በማለት ተከራክረዋል።
በተጨማሪ ፖሊስ በየጊዜው በሚመጡለት ጥቆማዎች ምክንያት ብቻ ደንበኞቻችን ያለአግባብ በእስር መቆየት የለባቸውም የሚል መከራከሪያ አንስተዋል።
ሀብት ለማጣራትና ንብረት ለማሳገድ ተብሎ በፖሊስ የቀረቡ ምክንያቶች የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ሆነው መቅረብ የለባቸውም የሚሉ የመከራከሪያ ነጥቦችንም አንስተው የፖሊስ ጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።
መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ጠበቆች ላነሱት የመከራከሪያ ነጥብ በሰጠው መልስ በተለይም ሰዎችን ገንዘብ በመቀበል ምንም አይነት ህጋዊ ሰነድ ያላሟሉ ሰዎችን ወደ ውጭ በማስወጣት እና ወደ ሀገር እንዳይገቡ የተከለከሉትን በማስገባት ሂደት ላይ፣ በሌላ መዝገብ ጉዳያቸው ከሚታዩ የስራ ኃላፊዎች በሚሰጥ መመሪያና ትዕዛዝ በቅንጅት የወንጀል ተሳትፎ ነበራቸው ብሏል።
የሁለት ተጠርጣሪዎች የውጭ ሀገር ዜጎች ናቸው ግንኙነት የላቸውም ተብሎ ለተነሳ መከራከሪያን በሚመለከት ፖሊስ በሕገወጥ ተግባር ላይ በቅንጅት ስራ ተሳትፎ መጠርጠራቸውን ገልጿል።
ጥቆማን በሚመለከት አሁንም እየቀረበ መሆኑን ገልጾ፤ በሚቀርቡ ጥቆማዎች መሰረት ማስረጃ የማሰባሰብ ስራ እንደሚከናወን ገልጿል።
ደንበኞቻቸው ማስረጃ የማጥፋት አቅም የሌላቸው መሆናቸውን የጠበቆችን መከራከሪያን በሚመለከት ፖሊስ የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች ቀደም ሲል በብሔራዊ መረጃ ደህንነት ሲሰሩ የነበሩና በሪፎርሙ ወደ ኢሚግሬሽን የተቀየሩ መሆናቸውን ጠቅሶ÷ ማስረጃ ሊጠፋ እንደሚችል በመግለጽ የዋስትና መብት ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል።
በዚህ የክርክር ሂደት ላይ በጠበቃ እና በመርማሪ በኩል የተስተዋሉ ለችሎቱ የማይመጥን ተገቢ ያልሆኑ ቃላቶች በድጋሚ እንዳይፀባረቁ እንዲታረም ችሎቱ አስገንዝቧል።
የግራ ቀኝ ክርክሩን በችሎት የተከታተለው እና የፖሊስ መዝገብን የመረመረው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ከሰዓት በኋላ በችሎት ተሰይሞ በመርማሪ ፖሊስ በኩል በተገቢ ጥረት ስራዎች መሰራታቸውን ከምርመራ መዝገቡ ማረጋገጡን አብራርቷል።
ከቀሪ የምርመራ ስራዎች አንጻር ተጠርጣሪዎቹ ቢወጡ ማስረጃ ይደናቀፋል የሚለውን ግምት በመያዝ፣ እንዲሁም ለምርመራው ውጤታማነት ቀሪ የምርመራ ስራ መሰራት እንዳለበት በማመን የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው በማለፍ ለፖሊስ የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል።
ውጤቱን ለመጠባበቅ ለሕዳር 7 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ