አቶ ታደሰ ካሳ በሌላ የክስ መዝገብ 8 ዓመት ከአምስት ወር እስራት ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የባህዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት በአቶ ታደሰ ካሳ ላይ በሌላ የክስ መዝገብ 8 ዓመት ከአምስት ወር ጽኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር መቅጣቱን አስታወቀ።
ችሎቱ ቅጣቱን ያሳለፈው ጥረት ኮርፖሬትን በዋና ስራ አስፈፃሚነት ይመራ በነበረበት ወቅት ከሌሎች ጋር በመተባበር ስራን በማያመች መንገድ መርተዋል በሚልና በተለያዩ የሙስና ክሶች ጥፋተኛ በመሆኑ ነው።
ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ ያቀረበባቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ ተከሳሹ ማስተባበል ባለመቻላቸው ቅጣቱ ሊወሰንባቸው ችሏል።
የተከሳሹን እድሜ፣ የጤና ሁኔታ፣ ህዝብንና ሃገርን ያገለገሉና፣ የቤተሰብ ሃላፊ መሆኑ በቅጣት ማቅለያነት በችሎቱ ተይዞላቸዋል።
ይህንኑ ማቅለያ በመያዝም ችሎቱ አቶ ታደሰ ካሳን በ8 ዓመት ከአምስት ወር ጽኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር መቅጣቱን አስታውቋል።
በዚሁ መዝገብ ከ3ኛ እስከ 9ኛ ያሉ ተከሳሾች ከሁለት ዓመት ከ6 ወር እስከ 3 ዓመት ከሰባት ወር እና ከአራት ሺህ እስከ 7 ሺህ ብር ቅጣት የተወሰነባቸው ቢሆንም፤ እስራቱ በ50 ሺህ ብር ዋስ በሁለት ዓመት እግድ ተቀይሮላቸው ከእስር እንዲለቀቁ ችሎቱ ወስኗል።
አቶ ታደሰ ካሳ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሚያዚያ 30/2012 ዓ/ም በዋለው ችሎት ከአቶ በረከት ስምኦን ጋር በተመሰረተባቸው ተመሳሳይ የሙስና ክስ 8 ዓመት ጽኑ እስራትና 15 ሺህ ብር መቀጣቱ ሲል ኢዜአ ዘግቧል።