Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያን እምቅ ሃብት የገለጡ እሳቤዎች …

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመሩ የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን መልክ በመግለጥ የቱሪዝም ገጽታን በመሠረታዊነት እየቀየሩ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በእነዚህ ሦስቱ ታላላቅ ፕሮጀክቶች አስደናቂ ታሪኳን፣ ታይተው የማይጠገቡ መልክዓ ምድሮቿን እና ህያው ባህሏን ለዓለም የገለጠች ሲሆን መዳረሻ ሆና ይበልጥ እንድትቀጥልም በቱሪዝም መሠረተ ልማት እየታነጸች ትገኛለች።

የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ቀድሞ በምትታወቅባቸው የቱሪዝም ሃብቶች ላይ ሌላ ተጨማሪ ጸጋን የጨመሩ ሆነዋል፡፡

ከአንድ ድንጋይ የተጠረቡትና የጠቢባን የእጅ ሥራ ማሳያ የሆኑት የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት በዓለም የምህንድስና ጥበብ ሚናችንን ያሳየንባቸው አሻራዎቻችን ናቸው፡፡

የጥያ ትክል ድንጋይ ታሪክ፣ ከሶፍዑመር ዋሻ እስከ ጎንደር የነገስታት ግንቦች፣ ከአክሱም ሐውልት እስከ ሐረር ግንብ ያሉ ሥራዎች ኢትዮጵያን የታሪካዊ፣ ባህላዊ እና የተፈጥሯዊ ቅርሶች ሀብታም ያደርጓታል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 19 የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶቿን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚ ሥፍራን ይዛለች፡፡

እነዚህ አቅሞች ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ገቢን በማሳደግ እና የሀገር ውስጥ ሀብትን በማንቀሳቀስ ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ።

ከዚህ በፊት በመሠረተ ልማት እጦት ተደብቀው የቆዩ መንፈስን የሚያድሱ የመስህብ ስፍራዎች፣ መልክዓ ምድሮች፣ የተለያዩ አዕዋፋት እና ዕጽዋት ትስስር ለጎብኝዎችና ለአሳሾች በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታን እየፈጠሩ ነው።

አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ ለማድረግ በተሠራው ሥራ ከተማዋ ውበት እንዲኖራት፣ ለነዋሪዎቿም ሆነ ለጎብኚዎች ምቹ እንድትሆን በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተተግብረዋል።

ከእነዚህም መካከል የገበታ ለሸገር መርሃ ግብር ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ይህ መርሃ ግብር የከተማዋን ወንዞች ከብክለት በማጽዳትና ዳርቻዎቻቸውን በማልማት፣ አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲናነቷን የሚመጥን የቱሪስት መስህብ ባለቤት እንድትሆን አስችሏታል።

በዚህም የአንድነት ፓርክ በታላቁ ቤተ መንግሥት ቅጥር ግቢ ውስጥ የሀገሪቱን ታሪክ፣ ባህልና የተፈጥሮ ሀብት በአንድ ላይ ይዞ ተገንብቷል፡፡ ፓርኩ የእንስሳት ማቆያ፣ የታሪክ ሙዚየምና የባህል ማዕከላትን አካትቷል።

ሌላኛው የገበታ ለሸገር ፕሮጀክት እንጦጦ ፓርክ ሲሆን ፓርኩ በእንጦጦ ተራራ ላይ የተገነባ ሲሆን ለስፖርት፣ ለብስክሌትና ለፈረስ ግልቢያ እንዲሁም ለተፈጥሮ ወዳጆች እጅግ የተመቸ ስፍራ ያደርገዋል።

ከተማዋን ከከፍታ ላይ ለማየት የሚረዱ የመመልከቻ ስፍራዎችና ማረፊያዎችም አሉት።

የወዳጅነት አደባባይ በአዲስ አበባ ከተማ እምብርት የሚገኝ ሲሆን የሰው ሰራሽ ሐይቅ፣ የውኃ ዳንስ እና ውብ የእግር ጉዞ መንገዶችን፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ማከናወኛዎችንና ትልልቅ የመዝናኛ ስፍራዎችን ያካተተ ነው።

ከገበታ ለሸገር በኋላ የመጣው የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማትም ከተማዋን በብዙ መልኩ ቀይሯታል፡፡ አዲስ አበባ ለእግረኛ፣ ለብስክሌተኛ፣ ለተሸከርካሪ ተጠቃሚ፣ ለስፖርት አዘውታሪ ሁሉ ተስማሚ፣ የጸዱ ወንዞች ባለቤት እንድትሆን አድርጓታል፡፡

ኢትዮጵያ በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና በገበታ ለትውልድ ውጥኖች የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት እና በአከባቢያቸው የሚገኙ ልዩ የተፈጥሮ ሀብቶችን አጉልተው እንዲያሳዩ በማድረግ በአጭር ዓመት ውስጥ እምቅ አቅሟን በመግለጥ ታሪክ ሰርታለች፡፡

መንግሥት ለተገበረው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምም ቱሪዝም አንዱ ምሰሶ መሆኑን አስመስክሯል፡፡

በገበታ ለሸገር የአዲስ አበባ እውነተኛ መልክ ኢትዮጵያውያንን በሚመጥን መልኩ የተገለጠ ሲሆን መንግሥት በገበታ ለሀገር የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ትልቅ ሥራ ሰርቷል፡፡

ብዙ ጎብኚዎችን በመሳብ፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን በማነቃቃት፣ የስራ እድሎችን በመፍጠር፣ መዳረሻዎችን በማልማት እና በማሻሻል እመርታ አሳይቷል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የገበታ ለትውልድ ውጥን አካል የሆኑት እና ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት የኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ፣ የሸበሌ ሪዞርት፣ ደንቢ ኢኮ ሎጅ እና የሐይቅ ሎጎ ሪዞርት ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡

በግንባታ ላይ ያሉ በርካታ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ሲበቁ ደግሞ የሀገራችንን ድንቅ የተፈጥሮ፣ የባህል እና መልክዓ ምድራዊ ውበት ይበልጥ የሚገልጡ ይሆናሉ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.