በአማራ ክልል ከ376 ሺህ ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ እንደሚከናወን ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በዘንድሮ የበጋ ወራት ከ376 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አልማዝ ጊዜው (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ የዘንድሮውን የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ ውጤታማ ለማድረግ ካለፉት ዓመታት ተግባራት ልምድ ተወስዶ እየተሰራ ነው፡፡
376 ሺህ 561 ሄክታር መሬት ላይ የተፈትሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው በ9 ሺህ 60 በተመረጡ ተፋሰሶች ላይ ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በየደረጃው የባለሙያ ስልጠናና የልማት መሳሪያ ልየታ ስራ እየተከናወነ መሆኑን በመግለጽ÷ ልማቱ ከጥር ወር 2016 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ይከናወናል ብለዋል፡፡
የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራውም ህዝቡን በማሳተፍ በአማካይ 23 ቀናት እንደሚከናወን ተናግረው፤ ከ307 ሺህ በላይ ቀያሽ አርሶ አደሮችና 273 ሺህ የቅየሳ መሳሪያ መለየቱን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ዘድሮው ለሚካሄደው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ሰው ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል፡፡
በሰብለ አክሊሉ