የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ብሔራዊ መግባባት እየፈጠረ ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ብሔራዊ መግባባትና ሀገራዊ አንድነት መፍጠር የሚያስችል ገንቢ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም ገለጹ፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ወጣቶች ከአካባቢያቸው ወጥተው ብሔራዊ አንድነት የሚፈጥሩበት የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት መርሐ-ግብር ማዘጋጀቱን አቶ ብናልፍ ገልጸዋል፡፡
በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያየ የሙያ መስክ የተመረቁ መሆናቸውን አስታውሰው÷ ከክልላቸው ውጭ በመሰማራታቸው ደስተኛ መሆናቸውን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን በተለያዩ ጉዳዮች በበጎ ፈቃደኝነት ለማገልገል ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በራሳቸው ፍላጎት የተመለመሉ ወጣቶች በተሰማሩባቸው አካባቢዎች ውጤታማ ስራ እያከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት በወጣቶች ዘንድ አብሮነትን በማጎልበት ለሀገራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባት ገንቢ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ነው ለኢዜአ የተናገሩት፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባትና ሀገራዊ አንድነት ለመፍጠር የወጣቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው÷ በሀገር ግንባታ ሂደት መንግስትና ሀገር የተለያዩ መሆናቸውን መረዳት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የሀገር ግንባታ በሂደት እንጂ በአንድ ወቅት የሚከናወን ባለመሆኑ ዜጎች ከልዩነት ይልቅ አንድነትና መግባባትን በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ አተኩረው መስራት እንደሚገባቸው አስረድተዋል፡፡
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩ ወጣቶች የተለያየ የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ የእምነት፣ ሙያና አካባቢ የተውጣጡ ቢሆንም ለኢትዮጵያ አንድነትና ብልጽግና በጋራ መቆማቸውን ነው የገለጹት፡፡
በመሆኑም የምንፈልጋትን የበለጸገች ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የወጣቶች የነቃ ተሳትፎ ቀጣይነት እንዲኖረው እየሰራን ነው፤ ተጠናክሮም ይቀጥላል ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!