Fana: At a Speed of Life!

ለኢትዮጵያ ብልፅግና ዕውን መሆን የሚተጋ ጠንካራ አመራር መፍጠር ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአመለካከትና የተግባር አንድነትን አስጠብቆ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና ዕውን መሆን የሚተጋ ጠንካራ የመንግስት አመራር መፍጠር ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

በሁሉም የኃላፊነት እርከን ላይ ለሚገኙ የመንግስት አመራሮች የሚሰጠው ስልጠና ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን÷ በመጭዎቹ ቀናትም ከ21 ሺህ 800 በላይ አመራር ወደ ስልጠና ይገባል ብለዋል።

ፓርቲው በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሕዝብ ይሁንታ ተመርጦ መንግስት በመመስረት የተቀበለውን ኃላፊነት ለመወጣት የአመራሩን አቅም ለማጎልበት እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በዚህም መንግስት ለሕዝብ የገባቸውን ቃሎች አፈጻጸም በመገምገም ጥንካሬዎችና ድክመቶችን መለየቱን ጠቁመው፥ እንደ ክፍተት የታዩትን ለመሙላትና አመራሩ በቀጣይ ውጤታማ እንዲሆን የፍላጎት ዳሰሳ ተደርጎ ስልጠና መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

አመራሩ ለተለዋዋጭ ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ሁኔታዎች እንዲዘጋጅ፣ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በብቃት እንዲወጣ የአቅም ግንባታ ስልጠናው ማስፈለጉንም ነው የተናገሩት።

የስልጠናው ዓላማ አመራሩን በእውቀት ማበልጸግ፣ የአገልጋይነት መንፈስና አስተሳሰብ እንዲላበስ ማድረግና ተልዕኮውን በብቃት እንዲወጣ የሚያግዝ ክህሎትን ማጎልበት መሆኑንም አብራርተዋል።

ለዚህም ከዕዳ ወደ ምንዳ በሚል ዐቢይ ርዕሰ ጉዳይ በተለያዩ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ጠቃሚ ሀሳቦችን የያዙ አጀንዳዎች መቀረጻቸውን ነው ያስረዱት።

በዚህም እስካሁን በሁለት ዙር በተሰጡ የከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ስልጠና ከ13 ሺህ 500 በላይ አመራር መሰልጠኑን ጠቅሰው፥ ከጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ከ21 ሺህ 800 በላይ የ3ኛ ዙር ሰልጣኞች ወደ ስልጠና እንደሚገቡ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የአመለካከት አንድነት በእቅዶች፣ በዓላማዎችና በመርሆዎች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር መሆኑን ያነሱት አቶ አደም፥ የተግባር አንድነት ደግሞ የተያዙ እቅዶችን በተቀራራቢ መንገድ እንዲፈጸሙ ማድረግ ነው ብለዋል።

ስልጠናው የአመራሩን አቅም በመገንባት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና እና የሀገር ግንባታ ጉዞን የሚያሳካ ጠንካራ መንግስት እንዲፈጠር ያስችላል ነው ያሉት።

አመራሩም በሀገርና ትውልድ ላይ ስጋት የሚሆኑ ጉዳዮችን ማስቀረትና የትናንት ወረትን ወደ ዛሬና ነገ ምንዳ የማሸጋገር ትልቅ የቤት ስራ እንዳለበትም አስረድተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.