በቀጣዩ አመት የተማሪዎች የምገባ መርሀግብር 600 ሺህ ተማሪዎችን ያካትታል- ኢ/ር ታከለ ኡማ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣዩ አመት የተማሪዎች ምገባ መርሀግብር 600 ሺህ ተማሪዎችን እንደሚያካትት ኢንጅነር ታከለ ኡማ ገለጹ፡፡
ኢንጂነር ታከለ ይህንን የተናገሩት በቴሌቪዥን እየተሰጠ ባለው “ትምህርት በቤቴ“ መርሀግብር በአጭር የፅሁፍ መልእክት ለተሳተፉና ጥሩ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ሽልማት በተበረከተበት ወቅት ነው።
ለተሸላሚ ተማሪዎች የላፕቶፕ ስጦታ የተበረከተ ሲሆን ልጆቻቸውን በጥንካሬ ለደገፉ ወላጆች የቴሌቪዥን ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።
ሽልማቱን ያበረከቱት ኢንጂነር ታከለ ኡማ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት መደበኛ የመማር ማስተማሩ ሂደት ቢስተጓጎልም ቴክኖሎጂን በተከተለና ተማሪዎችንም ባሳተፈ መልኩ የመማር ማስተማሩ መቀጠል ተችሏል ብለዋል።
ከዚያም ባለፈ በተያዘው አመት ለተማሪዎች የተደረገው ድጋፍ በቀጣዩ አመት በጥራትም በቁጥርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት፡፡
በዚህ አመት ለ3መቶ ሺህ ተማሪዎች እየተደረገ ያለው የተማሪዎች ምገባ መርሀ ግብር በቀጣዩ አመት 6መቶ ሺህ ተማሪዎች የሚካተቱበት ይሆናልም ነው ያሉት ።
በተማሪዎች ላይ የሚደረገው ኢንቨስትመንት ትውልድ መገንባት እንደመሆኑ ከጥቅሙ አንፃር ወጪው አነስተኛ መሆኑን አንስተው÷በተያዘው አመት ለተማሪዎች የተደረገው የዩኒፎርም፣የደብተር፣መማሪያ ቁሳቁስና የምገባ መርሀግብር በቀጣዩ አመት በጥራትም በቁጥርም ጨምሮ ይቀጥላል ብለዋል ።
ሽልማቱ የተበረከተላቸው በተለያየ የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ 41 ተማሪዎች መሆናቸውም ነው የተነገረው።
በአፍሪሄልዝ ቴሌቪዥንና ከአዲስ አበባ ት/ት ቢሮ ጋር በትብብር እየተሰራጨ ያለው “ትምህርት በቤቴ” መርሀግብር ከጠዋቱ 3 ሰአት እስከ ቀኑ 9:30 መተላለፉን ይቀጥላልም ነው የተባለው።
ተማሪዎች 8455 የአጭር የፅሁፍ መልእክት እየላኩ መሳተፍ እንደሚችሉ መገለጹን ከአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።