Fana: At a Speed of Life!

በብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በ42ኛው የዩኔስኮ ኮንፈረንስ ላይ እየተሳተፈ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) የተመራ ልዑክ በፈረንሳይ ፓሪስ እየተካሄደ በሚገኘው 42ኛው የተመድ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አጠቃላይ ኮንፈረንስ ላይ እየተሳተፈ ነው፡፡

በኮንፈረንሱ በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በዩኔስኮ ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ የብሔራዊ ፖሊሲ ንግግር እደሚቀርብ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው የሀገር መሪዎች፣ መንግሥትና ከፍተኛ የትምህርት ሚኒስትሮች የሚሳተፉበት ስብሰባ እና 13ኛው የወጣቶች መድረክ እንደሚካሄድ ተጠቅሷል፡፡

እንዲሁም በፈረንጆቹ 1972 የተደረገው የዓለም ቅርስ ኮንቬንሽን አባላት ጠቅላላ ጉባዔ በኮንፈረንሱ እንደሚጠበቅ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ከኮንፈረንሱ ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት እና ከዩኔስኮ አመራሮች ጋር በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡

በየሁለት ዓመቱ ከፈረንጆቹ ሕዳር 7 እስከ 22 ቀን 2013 የሚካሄደው ኮንፈረንሱ÷ በትምህርት፣ ሳይንስ፣ ባህል፣ ተግባቦት፣ መረጃና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የሰላም ባህል ለመገንባት፣ ድህነትን ለማጥፋትና ዘላቂ ልማትን ለማስፈን ለአባል ሀገራት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.