ኮሚሽኑ የተሳታፊዎች መረጣና የአጀንዳ ልየታ በክልሎች ማጠቃለል ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫው መሆኑን ገለፀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተሳታፊዎች መረጣ እና የአጀንዳ ልየታ በክልሎች ማጠቃለል ቀጣይ ትኩረት አቅጣጫው መሆኑን ገለፀ፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ተካሂዷል፡፡
በስብሰባው ከተያዙት አጀንዳዎች ውስጥ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ማዳመጥ ሲሆን÷ ሪፖርቱን ያቀረቡት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ሰብሳቢ መስፍን አርአያ (ፕ/ር) በ2016 በጀት አመት ኮሚሽኑ የሰራቸውን ስራዎችና ያጋጠሙ ችግሮች ለምክር ቤቱ አባላት አብራርተዋል፡፡
በገለፃቸውም÷ ኮሚሽኑ ቅድመ ዝግጅት፣ ዝግጅት፣ ትግበራ እና ክትትል በሚሉ ምዕራፎች ስራዎችን ከፋፍሎ መስራት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በቅድመ ዝግጅት ስራዎች አጠቃላይ ቢሮ ማደራጀት፣ የሰው ሃይል ማሟላት፣ ለስራው የሚያስፈልጉ ከአዋጁ በመነሳት ድንጋጌዎችን ማዘጋጀትና በየክልሉና ከተማ አስተዳደሩ በመሄድ የወደፊቱ ባለድርሻ አካላት የሚሆኑትን የመለየት ስራ መስራቱን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም የምክክር ሂደቱን ተግብረው የተሳካላቸውንም ሆነ ያልተሳካላቸው አለምአቀፍ ማህበረሰቦችን የማጥናት ሂደት እንደተከናወነም ተናግረዋል፡፡
በዝግጅት ምዕራፍ ደግሞ እንደገና ወደ የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እስከ ወረዳ ድረስ በመሄድ ባለድርሻ አካላትን በማግኘት ምን ይመስላሉ የሚለውን የመለየት ስራ መሰራቱንም ተናግረዋል፡፡
በየደረጃው ተገምግሞ ፀድቆ ወደስራ የገባ የምክክር ሂደቱ ስነ ዘዴ መኖሩን ጠቅሰው፤ በየጊዜው ስነ ዘዴው እየተፈተሸ እንደሆነ ገልጸዋል።
በዚህ መሰረት ከሚወከሉ ባለድርሻ አካላት 30 በመቶ የሴቶች ተሳትፎ መኖር አለበት ተብሎ እንደተቀመጠም ነው የተናገሩት፡፡
ሌላው በምክክር ኮሚሽኑ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ትኩረት መሰጠቱንም አንስተዋል፡፡
ባለፉት አራት ወራት እቅዳችን በስራቴጂያዊ ዕቅድ መሰረት ሶስት የትኩረት መስኮች አሉ ያሉት ዋና ሰብሳቢው፤ አንደኛው የላቀ ሃገራዊ ምክክር፣ በስራቴጂካዊ አጋርነት እና ትስስር እንዲሁም የላቀ የህዝብ ተሳትፎ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ውስጥ 11 ግቦች እና 18 ቁልፍ ተግባራት አሉት ብለዋል መስፍን አርዓያ(ፕ/ር)፡፡
ባለፉት ጊዜያት ከተሰሩ ስራዎች ውስጥም ከፌደራል ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመስማማት በየአካባቢው ቋንቋ ለተባባሪ አካላት ስልጠናዎችን መሰጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በአዲስ አበባ መስተዳድር፣ ጋምቤላ፣ በአፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ስልጠናው ተሰጥቷል ብለዋል፡፡
በዚህ በጀት አመት በአዲስ አበባ ከተማ እና በአራት ክልሎች 2280 ከዚህ ውስጥ ወንድ 2065 ሴት 215 ተባባሪ አካላት ተሳትፈዋልም ነው ያሉት፡፡
በቀጣይ የሀገራዊ ምክር ሂደት ተሳታፊዎችን መለየት ነው፤ ሂደቱም ከወረዳ ከየባለድርሻ አካላት ተሳታፊዎች ይመረጣሉ፣ ከዚያም ክልል ላይ ተገናኝተው አጀንዳ ይሰበሰባል ብለዋል፡፡
አጀንዳውም በአዋጁ መሰረት መሰረታዊ የሆኑ ላያግባቡን የቻሉ፣ ፈታኝ የሆኑ፣ ለግጭት የዳረጉን ምክንያቶች ተብለው የሚገመቱትን ውይይት ተደርጎ መሰብሰብ ነው፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ የማይጠቅም እና የሚጣል አጀንዳ አይኖርም ያሉት ሰብሳቢው፤ የሚመጡ አጀንዳዎች በሙሉ ክልል ላይ ይሰበሰባሉ ነወ ያሉት፡፡
በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ደግሞ እነዚሁ ከተማ አስተዳደሮች ላይ ይሰበሰባል፤ ከዚያም ወደ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይመጣሉ፤ ኮሚሽኑም የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን እንዲያጣራ ተናገግረዋል፡፡
ይህን ሲደርግ ብቻውን ሳይሆን 30 ከሆኑ እና ከመላ ሀገሪቱ ከተመረጡ አማካሪዎች ጋር መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ይህ ከሆነም በኋላ የዝግጅት ምዕራፍ ይጠናቀቃል፤ በቀጣይ የሀገራዊ ምክክሩን የማሳለጥ ስራው ይሰራል፤ በዚህም ስራ አወያይ አመቻች ይፈልጋል ብለዋል፡፡
እነዚህም ገለልተኛ መሆን ይኖርባቸዋል፤ ተገቢውን ስልጠና መውሰድ አለባቸው፤ የውይይቱን ርዕስ ተገንዝበው ሳያዳሉ የኮሚሽኑን አባላትን በማሳተፍ መፍትሄ የሚፈልጉ እና በተቻለ መጠን የውይቱቱ ሂደት ወደ መግባባት እንዲመጣ የሚያደርጉ ይሆናሉ ነው ያሉት፡፡
መግባባት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ ሌላ አማራጮች እንዲፈጠሩ በማድረግ ምክክሩ እንዲሳለጥ የሚያደርጉ መሆን ይኖርባቸዋልም ብለዋል፡፡
ከምክክሩ ሂደት በኋላ መግባባት በተደረሰባቸው ላይ ምክረ ሃሳቦችን በሚገባ ሰንዶ ለሚመለከተው አካል ይቀርባል ነው ያሉት፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የምክክር ኮሚሽኑ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች የተሳታፊዎች መረጣ እና የአጀንዳ ልየታ በክልሎች ማጠቃለል፣ የምክክር መድረኮችን የሚያሳልጡ አወያዮችና አመቻቾች ምልመላና ስልጠና ማካሄድ፣ መመሪያዎችን ማርቀቅና ማፅደቅ ናቸው ተብሏል፡፡
እንዲሁም ለስምሪት የሚሆን እቅድ ማውጣትና ሃብት ማፈላለግ፣ ሰፊ የህብረተሰብ ግንዛቤ ማስጨበጫ ክንውኖችን ማድረግ፣ ለሀገራዊ ምክክሩ አጀንዳ መቅረጽ፣ አሳታፊና አካታች ሀገራዊ ምክክር ማካሄድ ናቸው ነው የተባለው፡፡
በፌቨን ቢሻው