በኮምቦልቻ ጮሪሳ ጊዜያዊ ማቆያ የተሃድሶ ስልጠና ያጠናቀቁ ሰልጣኞች ወደ ሕብረተሰቡ ተቀላቀሉ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት ኮምቦልቻ ጮሪሳ ጊዜያዊ ማቆያ የተሃድሶ ስልጠና ያጠናቀቁ ሰልጣኞች ወደ ሕብረተሰቡ ተቀላቅለዋል፡፡
በተሀድሶ ሥልጠና ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው በአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ሰልጣኞች ገልጸዋል፡፡
ሰልጣኝ ወጣቶቹ በሰጡት አስተያየት÷በተሃድሶ ስልጠና ቆይታው በቂ ግንዛቤና እውቀት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
በቆይታቸው ለተደረገላቸው መልካም አያያዝ ያመሰገኑት ወጣቶቹ÷ ያገኙትን ትምህርት ተጠቅመው በሕብረተሰቡ ውስጥ ግንባር ቀደም የሰላም አምባሳደርና የልማት ተዋናይ ለመሆን መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡
ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ማስፈን በመንግስት ብቻ የሚከናወን ባለመሆኑም ሁላችንም ለሰላም ዘብ መቆም ይኖርብናል ሲሉ መልዕክት አስተላልፏል።
ከዛሬ ጀምረው ህብረተሰቡን በማስተማርና ግንዛቤ በመፍጠር ለሰላም ዘብ ለመቆም ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በፌዴራል ፖሊስ የሰሜን ምስራቅ ሪጅመንት አምስተኛ አዛዥና የኮምቦልቻ ጮሪሳ ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከል አስተባባሪ ም/ኮማንደር ኩራባቸው እንዳለ በበኩላቸው÷በማዕከሉ ታንፀው የሚወጡ ወገኖች ቀጣይ ለዘላቂ ሰላምና ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡ በሚያስችል አግባብ ግንዛቤ እየተፈጠረላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በየአካባቢያቸው ሲሄዱ ግንባር ቀደም የሰላም ተዋናይ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም መናገራቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡