Fana: At a Speed of Life!

የዓለም ባንክ የበረሃ አንበጣን ለመከላከል ለኢትዮጵያ የ63 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ፕሮግራም ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 14 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ የበረሃ አንበጣን ለመከላከል ለምታደርገው ጥረት የ63 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ፕሮግራም ይፋ አደረገ።

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ያፀደቀው ድጋፍ በሃገሪቱ የበረሃ አንበጣን ጨምሮ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የሚውል ነው ተብሏል።

ድጋፉ ባንኩ ምስራቅ አፍሪካን ጨምሮ በመካከለኛው ምስራቅና በተወሰኑ የደቡብ እስያ ሃገራት የበረሃ አንበጣን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ማስፈጸሚያ ያፀደቀው የ500 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ የበረሃ አንበጣ ምላሽ መስጫ ፕሮግራም አካል ነው።

ከዚህ ውስጥ 160 ሚሊየን ዶላሩ በመጀመሪያው ዙር ኢትዮጵያን ጨምሮ፥ ኬንያ፣ ጂቡቲ እና ኡጋንዳ የበረሃ አንበጣን ለመከላከል ለሚያደርጉት ጥረት ማስፈጸሚያ የሚውል ነው ተብሏል።

የአስቸኳይ ጊዜ የበረሃ አንበጣ ምላሽ መስጫ ፕሮግራሙ ለድሃና በአንበጣ መንጋው ለተጎዱ አርሶ እና አርብቶ አደሮች አስቸኳይ ድጋፍ ማድረግን ጨምሮ በአንበጣ መንጋው ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በማህበራዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ ማድረግን ያካትታል።

በዚህም ከ150 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች በመጭው የእርሻ ዘመን ምርታማነታቸውን ማሳደግ የሚያስችል የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ድጋፍ ይደረግላቸዋል።

ከዚህ ባለፈም ከ113 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ቤተሰቦች የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ አቅርቦትን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች የሚደረግላቸው ይሆናል።

በፕሮግራሙ መሰረት ኬንያ የ43፣ ኡጋንዳ 48 እንዲሁም ጂቡቲ የ6 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.