በሶማሌ ክልል የኮሌራ በሽታ እንዳይስፋፋ እየተሰራ ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)በሶማሌ ክልል እየጣለ ያለውን ዝናብ ተከትሎ የኮሌራ በሽታ እንዳይስፋፋ ህብረተሰቡን በማስገንዘብ የቅድመ መከላከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሀዋ ሱሌማን እንደገለጹት÷ በክልሉ ጅግጅጋ እና ቀብሪበያህን ጨምሮ በአምስት ከተሞች የኮሌራ ወረርሽኝ ተከስቷል።
በሽታውን ለመቆጣጠርም ቢሮው ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮዽያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከዓለም ጤና ድርጅት እና ከተባበሩት መንግስታት ህጻናት መርጃ ድርጅት(ዩኒሴፍ) ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በከተሞቹ በሽታው በ108 ሰዎች ላይ መከሰቱን የጠቆሙት ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ለሁሉም ሰዎች ተገቢው የሕክምና አገልግሎት መሰጠቱን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እየጣለ ያለውን ዝናብ ተከትሎ የኮሌራ በሽታ ይበልጥ እንዳይስፋፋ ህብረተሰቡን የማስገንዘብ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ለሕሙማን ተገቢው ሕክምና እየተሰጠ መሆኑንም ምክትል ቢሮ ሀላፊዋ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡