በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጣ የነበረ ከ500 ኪ.ግ በላይ ጫት ተያዘ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጣ የነበረ ከ500 ኪ.ግ በላይ ጫት መያዙን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አሥታውቋል፡፡
አገልግሎቱ ከጉሙሩክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ነው በኅገ-ወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሊወጣ የነበረውን ጫት የያዙት፡፡
በክትትሉም የአገልግሎቱ የአቪየሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ ኦፊሰሮች እና የቦሌ ዓየር መንገድ ቅርንጫፍ ባለሙያዎች ተቀናጅተው ክትትልና ፍተሻ በማድረግ መጥምረት መሥራታቸው ተገልጿል፡፡
ክብደቱ 509 ነጥብ 32 ኪ.ግ የሚመዝነው እርጥብ ጫት በ16 ሻንጣዎች ታሽጎ መነሻውን አዲስ አበባ አድርጎ በቦሌ ዓለም አቀፍ ዓየር ማረፊያ ወደ እንግሊዝ ለንደን ሊዘዋወር የነበረ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ከኮንትሮባንድ የጫት ምርቱ ጋር በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሥምንት የውጭ ሀገር ዜጎችም ጉዳያቸው በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እየተጣራ እንደሚገኝ የአገልግሎቱ መግለጫ ያሳያል፡፡