የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አንኳር ጉዳይ ብዝሀነትንና እኩልነትን ማስተናገድ ነው – አፈ-ጉባዔ አገኘሁ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አከባበር አንኳር ጉዳይ ብዝሀነትንና እኩልነትን ማስተናገድ ነው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ በሰጡት መግለጫም÷ 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በድምቀት እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡
በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች÷ ልምዳቸውን፣ ተሞክሯቸውንና ባሕላቸውን የሚለዋወጡበት፣ ዲሞክራሲያዊ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት፣ ለዘላቂ ሰላምና ለፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የሚነሳሱበት ነው ማለታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
ባለፉት 17 ዓመታት በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት፣ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አስተናጋጅነት በዓሉ ሲከበር÷ ሕዝቦች ይዘውት የቆዩትን አብሮነት እንዲያፀኑ፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን እንዲያጎለብቱ እና በሕገ-መንግሥቱና በፌዴራል ሥርዓቱ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲፈጠሩ የሚያስችሉ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል፡፡
በተከናወኑት ተግባራትም አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ነው ያነሱት፡፡
18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በሶማሌ ክልላዊ መንግሥት አስተናጋጅነት «ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት» በሚል መሪ ሐሳብ እንደሚከበር ጠቁመዋል፡፡
የዘንድሮው በዓል ሲከበርም ብዝኃነትን በማስተናገድና ኅብረ-ብሔራዊ ኢትዮጵያን በማጠናከር ሀገራዊ አንድነትን ለማስጠበቅ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚከናወንም ነው ያመላከቱት፡፡
የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ አንድነትን የሚያስጠብቁ አንኳር ተግባራት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ያሉት አፈ-ጉባዔው÷ በተለይም ለሀገር ኅልውና መከበር ሲባል አማራጭ የሰላም መንገዶችን ሁሉ መጠቀም ለምርጫ የማይቀርብ ተደርጎ እንደሚሠራ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
በዓሉም ከሕዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት አምስት ተከታታይ ቀናት የሚከበር ሲሆን÷ ሕዳር 25 የወንድማማችነት ቀን፣ ሕዳር 26 የአብሮነት ቀን፣ ሕዳር 27 የብዝኃነት ቀን፣ ሕዳር 28 የመደመር ቀን፣ ሕዳር 29 ደግሞ የኢትዮጵያ ቀን የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል በመግለጫቸው፡፡