በአማራ ክልል የተፈጠረውን አንፃራዊ ሰላም ዘላቂነት የሚያረጋግጥ ስራ መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ የገመገመና በቀጣይ አቅጣጫ ላይ የመከረ መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ሚኒስትር መለሰ ዓለሙን ጨምሮ የፌዴራል፣ የአማራ ክልልና የባህር ዳር ከተማ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡
አቶ መለሰ ዓለሙ÷ የአማራ ክልል ሰላማዊ ሆኖ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ወደነበሩበት ይመለሱ ዘንድ በጸጥታ አካላት እና በህዝቡ የተሰራው ስራ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
ህልውናችንን አስጠብቀንና እንደ ሀገር ፀንተን እንድንቆም ያደረጉንን እሴቶች ለመበጠስ ፅንፈኛው ኃይል እያደረገ ያለው ጥረት መቼውንም አይሳካም ብለዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ ልክ እንደሌሎች ህዝቦች በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራና ጥልቅ ዕምነት ያለው ህዝብ መሆኑን አውስተው÷በክልሉ የተፈጠረውን አንፃራዊ ሰላም ዘላቂነት የሚያረጋግጥ ስራ መስራት ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
በአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው÷ ለምንገኝበት አንፃራዊ ሰላም የሀገር ባለውለታ የሆነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ክቡር መስዕዋትነት ከፍሏል ብለዋል፡፡
በየደረጃው ያለው የክልሉ የፀጥታ መዋቅር ድርሻውን ተወጥቷል፣ ህዝባችንም ከጎናችን ሆኖ አግዞናል ማለታቸውን የፓርቲው መረጃ ያመላክታል።
ከተገኘው አንፃራዊ ሰላም ዘላቂነት ባሻገር የክልሉን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮቻችን ወደ የተሟላ እና መደበኛ ተግባር ውስጥ እንዲገቡ ለማድረግ የፖለቲካና የፀጥታ መዋቅሩን በመገምገም፣ በማደራጀትና አቅም በመገንባት ደረጃ ብዙ ስራዎች ተሰርተው ለውጥ መምጣቱን አንስተዋል፡፡
ህግ የማስከበርና ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ኃላፊነታችንን በአግባቡ በመወጣት ክልላችንን ወደተራዘመ ቀውስ እንዲገባ ለማድረግ እየሰራ ያለውን ፅንፈኛ ኃይል በአጭር ጊዜ መግታት ይጠበቅብናል ሲሉም ገልፀዋል።
ከአጎራባች ክልሎች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑ እና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመመለስ እየተካሄደ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑም ተጠቅሷል፡፡