ኮሚሽኑ በሶማሌ ክልል የተባባሪ አካላትና ተሳታፊዎች ልየታ ስራ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሶማሌ ክልል የተባባሪ አካላት እና ተሳታፊዎች ልየታ ስራ ጀምሯል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር መሀሙድ ድሪር÷ ኮሚሽኑ ለጀመራቸው ስራዎች ስኬታማነት በሶማሌ ክልል የተባባሪ አካላት እና የተሳታፊዎች ልየታ በይፋ መጀመሩን ገልጸዋል።
በሀገራዊ ምክክር የሚሳተፉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመምረጥ በሶማሌ ክልል ባሉ 11 ዞኖች ስር በሚገኙ 95 ወረዳዎችና 6 ከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ 824 ተባባሪ አካላት ተለይተዋል ብለዋል።
በኮሚሽኑ ለተለዩ ተባባሪ አካላት ከነገ ህዳር 4 ቀን 2016 ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የመጀመሪያ ዙር ስልጠና በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ተባባሪ አካላቱ ከስልጠናው በኋላ ወደየአካባቢያቸው በመመለስ ከአስተዳደር አካላት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከመንግሥት ሰራተኞች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከአርብቶና አርሶ አደሮች፣ ከእድር አባላት፣ ከአካል ጉዳተኞች፣ ከሴቶችና ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካይ እንደሚመርጡ አስታውቀዋል።
በየወረዳው የሚመረጡ አስር አስር ሰዎች ውስጥ ሁለት ሁለት በመምረጥ ክልሉን ወክለው አጀንዳዎቻቸውን በመያዝ በሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳተፉ ይደረጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ሂደቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ፣ በገለልተኝነትና በታማኝነት የሚከናወን በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም ኮሚሽነሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።