ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የሚበጅ ስራ እንዲያከናውን ሁሉም እንዲደግደፈው ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 4 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የሚበጅ ስራ እንዲያከናውን ሁላችንም ልንደግፈው ይገባል ሲሉ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ለተነሱ ጥያቄዎቭ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ኮሚሽኑ ይዞ የመጣውን ዕድል መጠቀም አለብን ብለዋል፡፡
በማብራሪያቸው “ይህ እድል ከባከነ መሰል እድሎችን ለማግኘት በርካታ ዓመታትን ሊፈጅብን ይችላል” ነው ያሉት፡፡
በ1953 ዓ.ም ለውጥን የመጠቀም እድል አግኝተን አምልጦናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በ1966 እንዲሁም በ1983 ዓ.ም ድጋሚ እድል አግኝተን አልተጠቀምንበትም ሲሉም አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም አሁን ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የሚሰጠንን እድል በተገቢው መልኩ መጠቀም አለብን ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
በተያያዘም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ በአማራና በትግራይ ክልል መካከል ጥያቄ የሚነሳባቸው ቦታዎች በሚመለከት ህግን የተከተለ፣ ዘላቂ ሰላምን ያከበረና የህዝብን አብሮነት ያስቀደመ የመፍትሄ አቅጣጫ እንከተል ብለን እየሰራን ነው ሲሉ አስረድተዋል።
“የእኛ ብቻ መፍትሄ ይተግበር አላልንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለዘላቂ ሰላምና ህዝቦች አብሮነት የሚሆን መፍትሄ ለሚያመጡ አካላት በራችን ክፍት ነው” ሲሉም ነው የተናገሩት።
“የእኛ ፍላጎት በሁለቱም ክልሎች መካከል ዘላቂ ሰላም ሰፍኖ ማየት ነው፤ የህዝቡም ፍላጎት ከዚህ የተለየ አይደለም” ሲሉም ተናግረዋል።