Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) መንግስት በአማራና በትግራይ ክልል መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ህዝበ ውሳኔን ማዕከል ያደረገ አካሄድ ጥሩ ነው ብሎ እንደሚያምን ገለፁ

 

አዲስ አበባ፣ ህዳር 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል መንግስት በአማራና በትግራይ ክልል መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ አንዱ ተረስቶ ሌላኛው አኩርፎ ቀጣይ ግጭት እንዳይፈጠር ህዝበ ውሳኔን ማዕከል ያደረገ አካሄድ ብንከተል ጥሩ ነው ብሎ ያምናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄዎች እየሰጡት ባለው ማብራሪያና ምላሽ፤ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች አንዳንድ አካባቢ እንዲሁም በየሰፈሩ በተለያዩ አካባቢያች ግጭቶች ይታያሉ ብለዋል፡፡

እነዚህ ግጭቶችም ከጉዟችን ያዘገዩናል ያሉ ሲሆን እኛ አብዝተን የምንሻው ሰላም ነው ብለዋል፡፡

የታጠቁ ሃይሎች ሰውን ይገድላሉ፤ ያሸብራሉ፤ እኛም ሀገር ሊኖር ይችላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያ ግን ወደ ድል አይወስድም፤ ለኢትዮጵያውያን ያለኝ ምክርም “በዶላር ከመገዳደል በሃሳብ መገዳደር ይሻላል” ነው ብለዋል፡፡

የኛ መሻትም ሰላም፣ ፍቅር እና ይቅርታ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ክላሽ አንግበው በየጫካው ላሉ ወንድሞቻችን ያለን መልዕክትም እባካችሁ ሰላምን ናቅ አናድርጋት የምትሻለው እሷ ናት ነው የሚለውን ነው ብለዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ÷ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዋና አላማው ህግ እና ስርዓትን ማስከበር መሆኑን ገልፀው፤ ይህም አንፃራዊ ሰላም አምጥቷል ብለዋል፤ ነግር ግን የተሟላ ሰላም አልመጣም ተጨማሪ ስራ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የሚነሱ የትኞቹም ጥያቄዎች የአንድ አካባቢን የሚያስደስቱ ሳይሆን ኢትዮያውያን የሚጠቅሙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል በአማራ እና በትግራይ አካባቢዎች ለሚነሱት ጥያቄዎች መንግስት ምላሽ እየሰጠ አይደለም ይባላል እኛ ግን እየሰጠን ነው ብለዋል፡፡

የፌደራል መንግስት “በአማራና በትግራይ ክልል መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ አንዱ ተረስቶ ሌላኛው አኩርፎ ቀጣይ ግጭት እንዳይፈጠር ህዝበ ውሳኔን ማዕከል ያደረገ አካሄድ ብንከተል ጥሩ ነው ብሎ ያምናልም ነው ያሉት፡፡

ይህንም ለሁለቱ ክልሎች አመራሮች በጋራ አወያይቷል፤ አቅጣጫ አስቀምጧል፤ እየሰራም ይገኛል፤ ህዝቡንም አወያይተናል፤ ምላሹንም እናቃለን ሲሉን ገልፀዋል፡፡

ነገር ግን ይህ መፍትሔ ብቸኛ ስላልሆነ የአማራ እና የትግራይ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሽማግሌዎች ተወያይተው ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ መፍትሄ አለው ካሉ እንቀበላለን ነው ያሉት፡፡

የእኛ ፍላጎት በሁለቱም ክልሎች መካከል ዘላቂ ሰላም ሰፍኖ ማየት ነው፤ የህዝቡም ፍላጎት ከዚህ የተለየ አይደለም ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.