የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የጋራ ተጠቃሚነትና ቀጣናዊ ትስስርን መሰረት ያደረገ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ህዳር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የጋራ ተጠቃሚነትና ቀጣናዊ ትስስርን መሰረት ያደረገ መሆኑን ሀገራት በቅጡ ሊገነዘቡት እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ÷ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ወደብ የማግኘት የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ጥያቄዋን በድርድር፣ በሰጥቶ መቀበልና በሰላማዊ አማራጭ የዲፕሎማሲ ጥረቷን አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን ከራስ ጥቅም አልፎ ለቀጣናው ሀገራት ዘላቂ ሰላምና የጋራ ተጠቃሚነት የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ለአካባቢው ሀገራት ሁለንተናዊ ትብብርና የልማት ትስስር እየሰራች መሆኑን ገልጸው÷ የባህር በር ጥያቄዋም በጋራ የመልማት ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መልካም ጉርብትናን፣ የጋራ ተጠቃሚነትን፣ አጋርነትንና ትብብርን መሰረት ያደረገ መሆኑን አንስተው፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ጎረቤት ሀገራትም ይሁን አጠቃላይ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በአዎንታዊ መልኩ ሊረዱት ይገባል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ በአካባቢው በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳታፊ መሆን አለባት ሲሉ ማንሳታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በቀይ ባህር አካባቢ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በአዎንታዊም ይሁን በአሉታዊ መንገድ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚነካ መሆኑን ገልጸው÷ በአካባቢው የሚደረግ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን ያገለለ ሊሆን አይገባም ነው ያሉት።