ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ተልዕኮውን አጠናክሮ ይቀጥላል – ሜ/ጄ ተሾመ ገመቹ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የህዝብን ሰላም የማስጠበቅ ተልዕኮውን በብቃት መወጣቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜ/ጄ ተሾመ ገመቹ ገለጹ።
ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራትና ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት መጠበቅም ያላትን ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥልም ተናግረዋል።
ሜጀር ጀኔራል ተሾመ ገመቹ÷ ሰራዊቱ ከምንጊዜውም በላይ የላቀ ወታደራዊ አቅም ፈጥሮ በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል ተደራጅቶ የሀገር አስተማማኝ አለኝታ ሆኖ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር ለማስከበር፣ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት እየተወጣ ያለ ብቁ ሰራዊት መገንባቱንም አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናዊና በዓለም ወታደራዊ ዲፕሎማሲ ቁልፍ ስፍራ እንዳላት ገልጸው፤ ከአፍሪካ እስከ ኮሪያ የዘለቀ የሰላም ማስከበር ወታደራዊ ተልዕኮው አሁንም በላቀ ብቃት ቀጥሏል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወታደራዊ ዲፕሎማሲ በመተማመንና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቅሰው÷ ከዚህ አኳያ ሰፋፊ ወታደራዊ የትብብር ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም የሀገርን ክብርና የተቋሙን ዝና ማጉላት እንደተቻለ እና የወታደራዊ ዲፕሎማሲ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ የጎረቤት ሀገራትና የቀጣናው ሰላም እንዲረጋገጥ አርዓያነት ያለው ተግባር በማከናወን ላይ እንደምትገኝም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ተምሳሌታዊ ወታደራዊ ተልዕኮ ከጎረቤት ሀገራት ባሻገር ዓለም የሚገነዘበውና የሚያደንቀው በመሆኑ ተልዕኮው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።