Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ለማቋቋም ድጋፍ ተደረገ

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያና የምስጋና መርሐ ግብር ላይ ለክልሉ ልማት ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል፡፡

መርሐ ግብሩ የፌደራል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ነው በወላይታ ሶዶ ከተማ የተካሄደው፡፡

በመርሐ ግብሩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ለማቋቋም የተለያዩ ክልሎች እና ግለሰቦች ድጋፍ አድርገዋል፡፡

በዚህም የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ÷ሁላችንም ተጋግዘን መልማት አለብን ያሉ ሲሆን ክልሉ እያደረገ ላለው የመደራጀት ስራም የኦሮሚያ ክልል 100 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን አብስረዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ÷የክልሉ ምስረታ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለማጎልበት የተሰሩ ስራዎች ማሳያ መሆኑን ገልጸው የሶማሌ ክልልም ለክልሉ 20 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ÷አብሮነት እና ህብረትን በማጠናከር በአዲስ ተስፋ በጋራ በመትጋት ለጋራ ስኬት እንሰራለን፤የአዲስ አበባ ከተማም ከክልሉ ጎን መቆሙን ለማሳየት የ60 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል ብለዋል፡፡

በም/ርእሰ መሥተዳድር ማእረግ የአማራ ክልል ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዱ ሁሴን በበኩላቸው÷የአማራ ክልል ከክልሉ ጋር በሁለንተናዊ ጉዞ አብሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠው ክልሉ 20 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን÷ክልሉ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎን መሆኑን ገልፀው፤ የ10 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን÷ክልላቸው ለአዲሱ ክልል ያለውን አጋርነት ገልፀው ለዚህም 10 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን አብስረዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ርእሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ÷አዲሱ ክልል ለመላው ኢትዮጵያ የመልማት ተስፋ ነው ፤ክልሉ ለሚያደርገው የልማት እንቅስቃሴ የሲዳማ ክልል ከክልሉ ጎን ነው ያሉ ሲሆን፤ ለዚህም 20 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርእሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር (ኢ/ር) የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን ካስተላለፉ በኋላ ክልሉ 15 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል ርእሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ÷የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ክልላቸው አጋርነቱን ለማሳየት የ5 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ÷ከአዲሱ ክልል ጋር በአንድነት በሁሉም መስክ በጋራ ለመስራት ቃል እንገባለን ያሉ ሲሆን÷ክልላቸው የ30 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን አብስረዋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁዋር÷ከተማ አስተዳደሩ ከክልሉ ጎን መሆኑን በመግለፅ የ10 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

በአጠቃላይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ይፋዊ የስራ ማስጀመሪያና ማብሠሪያ መርሐ ግብር ላይ ለክልሉ ልማት 580 ሚሊየን ብር ድጋፍ መደረጉ ተመላክቷል፡፡

 

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.