የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ-ወልዲያ የባቡር መስመር ዝርጋታ 93 በመቶ መድረሱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ-ወልዲያ የምድር ባቡር መስመር ዝርጋታ 93 በመቶ መድረሱን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡
የኮርፖሬሽኑ የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድና የ1ኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈፃፀም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተገምግሟል፡፡
አፈጻጸሙን የገመገመው ቋሚ ኮሚቴው ኮርፖሬሽኑ ያሉበትን ችግሮች ቀርፎ ከሂደት ይልቅ ውጤት ላይ በማተኮር ቀሪውን ሰባት በመቶ እንዲያጠናቅቅ አሳስቧል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ያለበትን የዕዳ ጫና በመቀነስ፣ የውስጥ ገቢንና የፋይናንስ አቅምን በማጠናከር የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በትኩረት እንዲሰራ ማሳሰቢያ መሰጠቱን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የመሬት አያያዝና አጠቃቀም እንዲሁም ከጥገና አገልግሎት መሣሪያዎች ጋር በተያያዘ ያሉበትን ክፍተቶች ለማረምም ከክልሎች እና ከተማ አስተዳዳሮች ጋር በቅንጅት መሥራት እንዳለበትም ቋሚ ኮሚቴው አስገንዝቧል።
የኮርፖሬሽኑ ቢዝነስ እና ዲቨሎፕመንት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌቱ ግዛው (ኢ/ር) በበኩላቸው÷ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት በንብረት ላይ ከፍተኛ ስርቆትና ውድመት በማድረሱ ሥራውን እንዳስተጓጎለው አስረድተዋል፡፡
አሁን ላይ በርካታ ንብረቶችን ማስመለስ ስለተቻለ ከአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ-ወልዲያ ያለውን ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ እንሠራለን ነው ያሉት፡፡
በኮርፖሬሽኑ የባቡር ኔትወርክ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሥላስ ካሣ (ኢ/ር)÷ በዕዳ እና በብድር ወለድ ጫና ምክንያት የቆሙ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ቋሚ ኮሚቴው እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለማስፋት ያለው የፋይናንስ ሁኔታ ጤናማ ባለመሆኑም ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም የግል ባለሀብቱን በማሳተፍ ተጨማሪ ፕሮጀክትን ለመሥራት መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ሽፋን 656 ኪሎ ሜትር መሆኑና በቀጣይ ወደ 1 ሺህ 266 ኪሎ ሜትር ለማድረስ መታቀዱም ተገልጿል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!