Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት ለማስፈን እየሠራሁ ነው – ብሔራዊ ባንክ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ2016 በጀት ዓመት ዕቅዱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል፡፡

የባንኩ ገዥ ማሞ ምኅረቱ የሦስት ዓመት (ከ2016 እስከ 2018) ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መገባቱን አስረድተዋል፡፡

የባንኩ ስትራቴጂካዊ የትኩረት መስኮች÷ የተረጋጋ የዋጋና ውጭ ዘርፍ እንዲኖር ማድረግ፣ በኢትዮጵያ የተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት ማስፈን፣ የፋይናንስ አካታችነት፣ ጥልቀትና ዲጂታይዜሽንን ማረጋገጥ እንዲሁም በባንኩ ውስጥ የአሠራር፣ የሰው ኃይል፣ የቴክኖሎጂ ልኅቀት ማምጣት እና ጠንካራ የመልካም አሥተዳደር ሥርዓት እንዲኖረው ማስቻል ናቸው ብለዋል፡፡

በእነዚህ አምስት ቁልፍ ዓላማዎች ላይ የተመረኮዘ የበጀት ዓመት ዕቅዱ ተዘጋጅቶ እየተሰራ እንደሆነ አብራርተው፤ አሁን ያለውን የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉን ዘመናዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

አሁን ያለውን የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ በዋጋ ላይ ወደ ተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ማሸጋገርን ቁልፍ ዓላማችን አድርገን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ አሥተዳደርና ሥርዓት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲኖር ማስቻል፣ የውጭ ምንዛሬ ሥርዓታችን ላይ የተለያዩ መመሪያዎችን ማሻሻል እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያ ክምችት አሥተዳደርን ማጠናከር ላይ ትኩረት ይደረጋል ሲሉ ጠቁመዋል።

የተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲኖር የተለያዩ ሥራዎች መከናወን እንዳለባቸው የገለጹት አቶ ማሞ÷ በፋይናንስ ሥርዓቱ ላይ ያሉትን የቁጥጥርና ክትትል መመሪያዎችን ማሻሻል፣ በፋይናንሻል ዘርፉ ላይ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንዲኖር ማስቻል፣ የባንኩን የገንዘብ አሥተዳደር ማሻሻል፣ የክፍያ ሥርዓቱን መሠረተ-ልማት ማሻሻል (ዲጂታል ፔይመንትን ማስፋፋት) የሚሉትን ለአብነት ዘርዝረዋል፡፡

እንዲሁም የፋይናንስ አካታችነት፣ ጥልቀትና ዲጂታይዜሽን ማረጋገጥን በተመለከተም÷ ሁለተኛውን የብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂና ከወለድ ነጻ ባንክ ማበረታታት፣ የፋይናንስ የትምህርትና የሸማቾች ጥበቃን ማጠናከር፣ አዲስ የኢንሹራንስ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ማቋቋም፣ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን አጠቃቀም ማሻሻል፣ የክሬዲት ሪፈረንስና የተንቀሳቃሽ ንብረት ምዝገባ መሠረተ-ልማት ማሻሻልን በልዩ ትኩረት የሚከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

የሦስት ዓመቱን ስትራቴጂክ ዕቅድ ሲዘጋጅ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ጨምሮ ዓለም አቀፋዊ ለውጦች፣  የቴክኖሎጂ ለውጥ፣  የጂኦ ፖለቲካ መሰነጣጠቅ እንዲሁም የኢትዮጵያ ውስጣዊ ሁኔታ የሚሉት መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

የባንኩ ስትራቴጂ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በማረጋጋት ላይ ትኩረት አድርጎ መዘጋጀቱንም ነው ያመላከቱት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.