በሕገ-ወጥ የወርቅ ግብይትና የውጭ ምንዛሬ ላይ በትኩረት እንዲሠራ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕገ-ወጥ የወርቅ ግብይትን እና የውጭ ምንዛሬን ከመከላከልና መቆጣጠር አኳያ በትኩረት እንዲሠራ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጠየቀ፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርትን ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል።
የብሔራዊ ባንክ አፈጻጸም ከተያዘው ዕቅድ አኳያ አበረታች መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡
የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ባንኩ በወሰዳቸው ሕጋዊ እርምጃዎች ለውጥ መታየቱን ያደነቀው ቋሚ ኮሚቴው፥ በቀጣይም የንረቱን መጠን ዝቅ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሆኖ በልዩ ትኩረት የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ አሳስቧል፡፡
ሕገ-ወጥ የወርቅ ግብይትን በመከላከልና በመቆጣጠር ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባውን የወርቅ መጠን ከማሣደግ አኳያም በቀጣይ ባንኩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባባር በትኩረት እንዲሠራ ተጠይቋል፡፡
ከሕገ-ወጥ የውጭ ምንዛሬ ጋር በተያያዘም የተጀመሩ ሥራዎችን በማጠናከር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
ተንቀሳቃሽ ንብረትን በማስያዝ ብድር መፈቀዱ የሚበረታታ በመሆኑ አሁን በአንድ ክልል የተጀመረው ወደ ሌሎች ክልሎችም የሚሠፋበት ሁኔታ እንዲኖር ቋሚ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው