Fana: At a Speed of Life!

በጎርፍ አደጋ የተጎዱ ዜጎችን ለመርዳት የሚደረገው ጥረት ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎርፍ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችን ለመርዳት የሚደረገው ጥረት ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተ/ማሪያም እና በኢትዮጵያ የተመድ ዋና ተወካይና የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር) በጉዳዩ ላይ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም÷ በቅርቡ በኢትዮጵያ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚገመቱ ዜጎች ጉዳት እንደደረሰባቸው አንስተዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ 600 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች በጎርፋ አደጋ ምክንያት ከመኖሪያ ቀዬአቸው መፈናቀላቸው ነው የተገለጸው፡፡

የጎርፍ አደጋው በ7 ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 85 ወረዳዎች ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን÷ ጉዳት ከደረሰባቸው ዜጎች ውስጥ 80 በመቶዎቹ በሶማሌ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡

በአምባሳደር ሽፈራው እና ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክም በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች በመጎብኘት የሰብዓዊ እርዳታ ማዳረስ የሚቻልባቸው ሁኔታዎችን ተመልክቷል፡፡

አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ከአጋር አካካት ጋር በመቀናጀት ለተጎጂዎቹ ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ እርዳታ እያቀረበ መሆኑ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

ከእርዳታው በተጨማሪም መንግስት የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ መከላከያ ሰራዊት፣ ሄሊኮፕተር እና ጀልባዎች ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች በማሰማራት የጎርፍ አደጋው የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ጥረት እያደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለው የሰብዓዊ እርዳታ ሥርጭት በአቅም ውስንነት እና በተለያዩ ምክንያች በቂ አለመሆኑ ነው የተጠቆመው፡፡

ለአብነትም በሶማሌ ክልል በአደጋው ጉዳት ከደረሰባቸው ዜጎቸ ውስጥ 10 በመቶ የሚሆኑት ብቻ እርዳታ እያገኙ መሆኑ ተነስቷል፡፡

አደጋው ነዋሪዎችን ከቀዬአቸው ከማፈናቀል ባለፈ በጤና፣ በመሰረተ ልማት እና በሌሎች ዘርፎች ላይ ጉዳት ማድረሱን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

ስለሆነም ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች አስፈላጊውን የሰብዓዊ እርዳታ ለማዳረስ በሀገር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ አስቸኳይ ተጨማሪ የሰብዓዊ እርዳታ በማሰባሰብ የሚሰጠውን ምላሽ ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድጅቶችም ለተጎጂዎቹ እርዳታ ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ ጥሪ ቀርቧል፡፡

ከዚህ ባለፈም በአካባቢዎቹ የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል መፍትሔ ለማበጀት የገንዘብ ድጋፍ ማፈላለግ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.