Fana: At a Speed of Life!

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው ተባለ

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ያሉ የቱሪዝም ጸጋዎችን በማልማት እና በማስተዋወቅ ክልሉ የቱሪዝም ማዕከል እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተልጿል፡፡

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል መንገሻ÷ በክልሉ የሚገኙ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስሕቦችን በማልማት የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ይሰራል ብለዋል።

ክልሉ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የላቀ የቱሪዝም አገልግሎትና የጎለበተ የባህል እሴት ለመፍጠር እቅድ አውጥቶ ወደ ተግባር መግባቱን አስረድተዋል።

የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን በማነቃቃት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ሃላፊው አብራርተዋል።

ክልሉ በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች ስላሉት ከህዝቡ የመልማት ፍላጎት እና የቱሪዝም ኢንዱስትሪው መሸከም ከሚችለው አቅም አንጻር ሰፊ የስራ እድል መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቡቶ አኒቶ በበኩላቸው÷ በክልሉ ያሉትን የቱሪዝም ሃብቶች በማልማት እና በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

ቱሪዝም ኢኮኖሚን በላቀ ደረጃ ማነቃቃት የሚያስችል አቅም አለው ያሉት አፈ ጉባኤው÷ ያሉትን የተፈጥሮ፣ ባህላዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች ማልማት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ያሉትን ሃብቶች ከማልማት በተጓዳኝ ቱሪዝምን ማስተዋወቅ ለዘርፉ እድገት የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት መጥቀሳቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

የክልሉ የባህል እና ቱሪዝም ቢሮ የ2016 የሴክተር ጉባዔ በየም ዞን ሳጃ ከተማ እየተካሔደ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.