Fana: At a Speed of Life!

የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ 7 ተከሳሾች ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዚዳንትር ጫላ ዋታ (ዶ/ር) ጨምሮ 7 ተከሳሾች በተከሰሱበት ከባድ የሙስና ወንጀል ላይ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ውድቅ ተደረገ።

ተከሳሾቹ በክስ ዝርዝሩ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ገልጸው÷ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ባጠቃላይ 15 ተከሳሾች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክሶችን መመስረቱ ይታወሳል።

ከ1ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር ያሉት ተከሳሾች የዩኒቨርሲቲው አመራርና የማኔጅመንት አባል በመሆን ሲሰሩ የመንግስት ግዢ አዋጅን በመተላለፍ በ2012 ዓ.ም በያዙት ቃለ ጉባዔ መሰረት ሕግን ባልተከተለ መልኩ ያለአግባብ ቢኤች ዩ ለተባለ አማካሪ ግዢው በቀጥታ እንዲፈጸም በማኔጅመንት ውሳኔ ማስተላለፋቸው በክሱ ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም ዩኒቨርስቲው ውል ሲዋዋል ዩኒቨርሲቲውን በመወከል የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት 1ኛ ተከሳሽ ውል ሰጪ ሆነው፣ 7ኛ ተከሳሽ ውሉን በመፈረም በ5ኛ ተከሳሽ ትዕዛዝ መሰረት በ1ኛ ተከሳሽ ስም ለተመዘገበው አማካሪ ድርጅት ያለአግባብ ክፍያ እንዲፈጸም መደረጉ ተጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል የዩኒቨርሲቲውን የመተዳዳሪያ እና የግዢ አዋጁን በመተላለፍ የ14 ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ግዢ በመፈጸም 116 ሚሊየን 389 ሺህ 964 ብር ማሽነሪዎችን በስጦታ ያገኙ በማስመሰል 12ኛ፣ 13ኛ እና 14ኛ ተከሳሾች በተሽከርካሪ ግዢ ያለአግባብ ጥቅም ማግኘታቸው በክሱ ተብራርቷል።

እንደ አጠቃላይ ተከሳሾቹ በሰኔ 10 ቀን 2012 ዓ.ም በቀጥታ ግዢ እንዲፈጸም ውሳኔ በማስተላለፍ ከሌሎች ተከሳሾች ከስራ ተቋራጮች ያለአግባብ ካለ ግልፅ ጨረታ ግዢ በመፈጸም በመንግስት ላይ 195 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ሲል ዐቃቤ ሕግ በዋና በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆን ስልጣንን ያለአግባብ በመገልገል ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

ከተከሳሾቹ መካከል አንደኛ ተከሳሽ ጫላ ዋታ (ዶ/ር) ጨምሮ 7 ግለሰቦች ብቻ ከማረሚያ ቤት ቀርበው የተመሰረተባቸው ዝርዝር ክስ በችሎቱ እንዲደርሳቸው ተደርጎ ክሱ በንባብ ተሰምቷል።

ተከሳሾቹ በጠበቆቻቸው አማካኝነት የቀረበባቸው ክስ ዝርዝር ፍሬ ነገሩ እንዲሻሻልላቸው የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ አቅርበዋል።

ዐቃቤ ሕግም የክሱ ግልጽነት በመጥቀስ ክሱ ሊሻሻል አይገባም በማለት በጽሁፍ መልስ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱም መርምሮ ክሱ እንዲሻሻል የቀረበው ጥያቄ አግባብ አይደለም በማለት የክስ መቃወሚያ ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ ብይን ሰጥቷል።

ከብይኑ በኋላ ተከሳሾቹ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደርጎ ሰባቱም ተከሳሾች በክስ ዝርዝሩ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ገልጸው፤ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ዐቃቤ ሕግም ተከሳሾቹ ክደው ቃላቸውን የሰጡ በመሆኑ ምስክሮቹ እንዲሰሙለት በመጠየቅ፤ አጠቃላይ 21 ምስክሮች እንዳሉት ለችሎቱ ገልጿል።

ፍርድ ቤቱም ፖሊስ ለዐቃቤ ሕግ ምስክሮች መጥሪያ እንዲያቀርብ በማዘዝ ምስክሮችን ለመስማት ለታህሳስ 22 እና ለታህሳስ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.