Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የወባ በሽታን ለመከላከል የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ ነው

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የወባ በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል የጸረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ከሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ የተለያዩ የጤና ተቋማት በተካሄደ ምርመራ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ሰዎች የወባ በሽታ ተገኝቶባቸው በወቅቱ ህክምና እንዲያገኙ መደረጉን ኢንስቲትዩቱ ጠቅሷል።

በኢንስቲትዩቱ የወባ ማስወገድ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዳምጤ ላንክር እንደገለጹት÷ ወባ ከተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ 75 በመቶ በማዕከላዊ፣ ምዕራብና ሰሜን ጎንደር ዞኖች እንዲሁም በባህርዳርና ዙሪያዋ በሚገኙ 30 ወረዳዎች ነው።

በወቅታዊ ችግር ምክንያት ከሁሉም አካባቢ ሪፖርት ማምጣትና የአካባቢ ቁጥጥር ስራ መከናወን እንዳልተቻለ አመልክተዋል።

ሆኖም በክልሉ እየተቆራረጠ በቀጠለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ጋር ተያይዞ የወባ በሽታ ስርጭት እንዳይጨምር ለመከላከል የሚደረገው ጥረት መቀጠሉን አስተባባሪው አስረድተዋል።

በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠርም በ43 ወረዳዎች ውስጥ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ የጸረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት ለማካሄድ ታቅዶ በ27 ወረዳዎች ስር በሚገኙ 190 ቀበሌዎች ርጭት መከናወኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በርጭቱም ከ18 ነጥብ 3 ሚሊየን ካሬ ሜትር በላይ ውሃ ያቆሩ አካባቢዎችን መድረስ መቻሉን ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ ባለፉት ዓመታት የተሰራጩ አጎበሮችን በአግባቡ በመጠቀም፣ ለውሃ መራቢያ የሆኑ አካባቢያዎችን በማጽዳትና ህመም ሲሰማው ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ጤንነቱን እንዲጠብቅ አቶ ዳምጤ መልዕክት አስተላልፈዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.