በስለት በማስፈራራት ንብረት የዘረፉ ተከሳሾች በጽኑ እስራት ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተሳፈረችበት በተለምዶ ባጃጅ እየተባለ በሚጠራው ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ ውስጥ በስለት አስፈራርተው ንብረቷን ዘርፈው የተሰወሩ ሦስት ተከሳሾች በዘጠኝ ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጡ።
የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሾቹ 1ኛ አብዲ ጌታቸው፣ 2ኛ ሳላ ጣሶ (በቅጽል ስሙ ሄኖክ) እና 3ኛ ኢሳ ሀብታሙ (በቅጽል ስሙ ናትናኤል) ናቸው።
በሸገር ከተማ የሰበታ ክፍለ ከተማ ምድብ ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ከባድ የውንብድና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸው ነበር።
በክሱ እንደተመላከተውም÷ ተከሳሾቹ ሰኔ 24 ቀን 2015 ዓ.ም ከረፋዱ 4:00 ከሰበታ ከተማ ታክሲ ተራ አካባቢ መነሻዋን አድርጋ በባጃጅ ተሽከርካሪ የተሳፈረችውን ሒሩት መገርሳ የተባለች የግል ተበዳይን በስለት በማስፈራራት ወደ ፉሪ የባቡር ሃዲድ አስገድደው ወስደዋታል፡፡
በያዙት ስለትም አንገቷ ላይ ጉዳት በማድረስ 12 ግራም ወርቅ የአንገት ሀብል፣ አምስት ግራም ወርቅ የጣት ቀለበት፣ ላፕቶፕ ኮምፒዩተርና የእጅ ስልኳን ጨምሮ በአጠቃላይ 145 ሺህ 750 ብር የሚገመት ንብረቷን ወስደው ጫካ ውስጥ ጥለዋት መሰወራቸው በክሱ ተመላክቷል።
በሰበታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ አባላት በተደረገ ክትትልም ተከሳሾቹ ከተሰወሩበት በቁጥጥር ስር ውለው የምርመራ ማጣሪያ ተደርጎባቸዋል።
ተከሳሾቹም በችሎት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው ተደርጎ በችሎት በንባብ ከተሰማ በኋላ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ዐቃቤ ሕግም ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ የግል ተበዳይን ጨምሮ አምስት ምስክሮችን አቅርቦ አሰምቷል።
የምስክር ቃል የመረመረው ችሎቱ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ከባድ የውንብድና ወንጀል ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።
ይሁንና ተከሳሾቹ በተገቢው መከላከል ባለመቻላቸው እያንዳንዳቸው እንዲከላከሉ በተባሉበት ድንጋጌ የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጥቶባቸዋል።
በዚሁ መሠረት ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየትን መርምሮ እያንዳንዳቸው በዘጠኝ ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ዛሬ በነበረው ቀጠሮ ወስኗል።
የሸገር ከተማ ማረሚያ ቤት የተከሳሾቹን ቅጣት እንዲያስፈጽም ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ