Fana: At a Speed of Life!

በአቪዬሽን ዘርፉ በዘላቂነት ተወዳዳሪ ለመሆን የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ አቅምን ማሳደግ ይገባል ተባለ

 

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአቪዬሽን ዘርፉ በዘላቂነት ተወዳዳሪ ለመሆን የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ አቅምን ማሳደግና ጠንካራ ኢንዱስትሪ መፍጠር አለብን ሲሉ የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግስቴ ተናገሩ።

በሳይንስ ሙዚየም ከተከፈተው የመጀመሪያው የአቪዬሽንና ኢኖቬሽን ኤክስፖ ጎን ለጎን ሲምፖዚየም እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ ላይ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር)÷ አንድ ምዕተ ዓመት ያስቆጠረ የአቪዬሽን ታሪክ ይዘን ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ላይ በተፈለገው ልክ አልሰራንም ብለዋል።

ለዚህም ባለፉት ስርዓቶች ለኢንዱስትሪው የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን፣ በስርዓት ተደግፎ አለመመራቱ እና ባለቤት አልባ መሆኑን እንደ ምክያት አንስተዋል።

አሁን ላይ ኢንዱስትሪውን የሚያበረታቱ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጠቅሰው÷ ይህም በቀጣይ ለመገንባት ለምናስበው የኢኖቬሽን ዕድገት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግስቴ÷በዘርፉ በዘላቂነት ተወዳዳሪ መሆን የሚቻለው የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ አቅማችንን እና አጠቃቀማችንን ማሳደግ እንዲሁም ጠንካራ ኢንዱስትሪ መፍጠር ስንችል ነው ብለዋል።

ለዚህም በኤክስፖው የቀረቡ የፈጠራ ውጤቶች ትልቅ መነሳሳትን እና ተስፋን የሚያጭሩና ለአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ዕድገት ትልቅ አስተዋፅዖ የሚያደርጉ ወጣቶችን የተመለከትንበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በኤክስፖው ላይ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የፈጠራ ውጤቶች የቀረቡ ሲሆን፤ የፈጠራ ውጤቶች ውድድር ተካሂዶ ለአሸናፊዎች የተለያዩ ሽልማቶች እና ድጋፎች ተበርክተዋል።

በመራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.