ለኢትዮጵያ ህዝብ አለኝታ የሆነ ዓየር ኃይል እየገነባን እንገኛለን – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለኢትዮጵያ ህዝብ አለኝታ የሆነ ኢትዮጵያን የሚመጥን ዓየር ኃይል እየገነባን እንገኛለን ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
በቢሾፍቱ በሚገኘው የዓየር ኃይል መኮንኖች ክበብ የዓየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አካል የሆነ የፓናል ውይይት ሲጠናቀቅ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የማጠቃለያ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም፤ በ27 ዓመት መገንባት ያልተቻለን ዓየር ኃይል በ3 ዓመት የውጊያ ዝግጁነቱ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን የሚመጥን አድርገን እየገነባን እንገኛለን ብለዋል።
አፄ ኃይለሥላሴ በአፍሪካ አለ የሚባል የተደራጀ ዓየር ኃይል በመገንባት መሠረት እንደጣሉና የደርግ መንግስትም ወታደራዊ ስለነበረ አየር ኃይልን በአፍሪካ ደረጃ በማይታመን ሁኔታ መገንባቱንም አንስተዋል።
በእርስ በርስ ግጭት እና በፖለቲካ ሽኩቻ ወደ ስልጣን የመጣው የኢህአዴግ መንግስት ዓየር ኃይልን እንዳልነበረ አድርጎ አፍርሶታል ብለዋል።
ይህ መሆኑም ሀገርን ከጥቃት የሚከላከል ዓየር ኃይል እንዳይኖረን አድርጎ ቆይቷል ብለዋል።
በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የፈረሰውን ዓየር ኃይል መልሶ ለማደራጀት የተሞከረ ቢሆንም በመንግስት ደረጃ ትኩረት በመነፈጉ መድረስ በሚፈለግበት ደረጃ መድረስ አልቻለም ሲሉም ተናግረዋል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተሠራው ሪፎርም መሠረት ሰራዊት ብሔር የለውም በሚል ከፖለቲካ ወገንተኝነት እና ብሔርተኛነት የፀዳና የሀገር ፍቅር ያለው ኢትዮጵያን የሚመጥን ሠራዊት እየገነባን እንገኛለን ብለዋል።
ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ መሠረት በማድረግ ፕሮፌሽናል ሠራዊት እየገነባን ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ÷ በውጭ ጠላቶቻችን የሚላላኩ ቅጥረኛ ኃይሎች እርስ በርስ እንድንገዳደል ቢያደርጉም ለመጪው ትውልድ የሚተርፍ መከላከያ ኃይል እየገነባን እንገኛለን ሲሉ ገልፀዋል።
ዓየር ኃይል የዘመኑን የውጊያ ትጥቅ የታጠቀ የውጭም ይሁን የውስጥ ጠላቶችን የሚመክት የህዝብ አለኝታ ሆኖ እንዲቀጥልም እየተሠራ መሆኑን መናገራቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡