Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልልን የብጥብጥና የሁከት ማዕከል ለማድረግ የተቀናጀ ሥራ እየተሠራ በመሆኑ ሕዝቡ አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ ጥሪ ቀረበ

 

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልልን የብጥብጥ እና የሁከት ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል ተደጋጋሚ የሕገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር በቁጥጥር ስር ውሏል።

የአማራ ክልልን ወቅታዊ የፀጥታ ችግር ታሳቢ ያደረጉ እና በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የሕገ ወጥ መሳሪያዎች ዝውውር በፀጥታ ኃይሉ ጥብቅ ቁጥጥር መያዛቸውን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ለአሚኮ በላከው መረጃ አስታውቋል።

የሕገ ወጥ መሳሪያ እና ተተኳሽ ዝውውሩ ከሰሞኑ በተደጋጋሚ መከሰቱም ተመላክቷል።

መነሻውን መቀሌ ከተማ ያደረገ እና ሲሚንቶ ከጫነ ተሽከርካሪ ላይ የተጫነ ሕገ ወጥ ተተኳሽ በፍላቂት ገረገራ ከተማ አስተዳደር ፖሊሶች ጥብቅ ክትትል ተይዟል። 10 ሺህ 385 የክላሽ እና የብሬን ተተኳሽም ተይዟል።

በሌላ በኩል ከሀራ ተነስቶ ቆቦ ሁለት ቀናትን በማደር፤ ጋይንት ደርሶ ዛሬ ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ላይ ከጋይንት ተነስቶ ወደ ደብረ ታቦር ከተማ ሲደርስ በተደረገ ፍተሻ ሰባት ክላሽ እና 2009 ጥይት ተይዟል። ተጠርጣሪው በሰጠው መረጃ በፍተሻ ወቅት ያልተያዘ ተጨማሪ 15 ሺህ ጥይትም ካስቀመጠበት አሳይቷል።

አንድ ሲኖ ትራክ የመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካን ምርት ጭኖ ከቆቦ መስመር ወደ ደብረታቦር ሲመጣ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ሲሚንቶው ውስጥ 18 ሺህ 143 ጥይት በፍተሻ ተይዟል።

በተመሳሳይ አሸዋ ጭኖ ከቆቦ ወደ ጋይንት መስመር ሲጓዝ በደረሰ ጥቆማ በርካታ ሕገ ወጥ ተተኳሾችን እና የኮንትሮባንድ እቃዎችን እንደጫነ በቁጥጥር ስር ውሏል ተብሏል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም የአማራ ክልልን የብጥብጥና የሁከት ማዕከል ለማድረግ የተቀናጀ ሥራ እየተሠራ በመሆኑ ሕዝቡ አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ጥሪ አቅርቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.