ኢትዮጵያ የባህር ወደብ ተጠቃሚ የሚያደርጋትን ስምምነት መፈረሟ ፍትሃዊ ተጠቃሚነቷን የሚያረጋግጥ ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የባህር ወደብ ተጠቃሚ የሚያደርጋትን ስምምነት መፈረሟ ፍትሃዊ ተጠቃሚነቷን የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ም/ቤት አፈ-ጉባኤ ተመስገን ዲሳሳ (ዶ/ር) እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር ተናገሩ፡፡
ኢትዮጵያ ከ30 ዓመታት በኋላ የወደብ ባለቤትነት ስምምነት መፈረሟን አስመልክቶ በአሶሳ እና በድሬዳዋ ከተማ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።
በመርኃ ግብሩ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ም/ቤት አፈ-ጉባኤ ተመስገን ዲሳሳ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልእክት፤ ይህን ታሪካዊ የመግባቢያ ሰነድ ኢትዮጵያ መፈረሟ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ጤናማ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያሳያል ብለዋል፡፡
የሰጥቶ መቀበል መርህን የተከተለ የሌላኛውን ጥቅም በማይነካ፣ የደህንነት መውጫ፣ የሠላም እና አንድነት መገለጫ መግባቢያ ነው ሲሉ ማከላቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመልክቷል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ከፍታ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ለጋራ ተጠቃሚነት በትብብር መስራት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
ብዝሃነትን፣ አንድነትን እና ፍቅርን በማጠናከር ሁሉም ሀገራዊ ኃላፊነቱን ይወጣ ያሉት ከንቲባው፤ በፍጥነት እያደገ የሚገኘውን ኢኮኖሚ ከማስተናገድ፣ ከሰላም፣ ደህንነትና ከህዝብ ቁጥር አንፃር የባህር በር ማግኘት ወሳኝ ነዉ ሲሉ መናገራቸውን የድሬዳዋ ኮሙኒኬሽን መረጃ ጠቅሷል።
በተመሳሳይ በደሴ ከተማ በተካሄደ የደስታ መግለጫ ሰልፍ የኢትዮጵያን የወደብን ፍላት ጥያቄ የሚመልስ ስምምነት ላይ መድረሱ እንዳስደሰታቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ኢትዮጽያ ከሶማሌ ላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት ሀገራዊ ጠቀሜታው የላቀ ነውም ብለዋል።
በወደብ እጦት ምክንያት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ወጪ ታወጣ እንደነበረው አስታውሰው፤ ስምምነቱ ይህንን ጫና እንደሚቀንስ እምነታቸውን ገልጸዋል።
ስምምነቱ ለሀገራዊ ትብብርም የተሻለ ግንኙነትን እንደሚፈጥርና ቀጠናዊ ትብብርን እንደሚያሳድግ መግለጻቸውን አለባቸው አባተ ዘግቧል።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- FBC(Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!