በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁለተኛው ትውልድ የተደረገው ጥሪ ሀገርን ለማወቅ እድል ይፈጥራል – መሐመድ አል አሩሲ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁለተኛ ትውልድ ያቀረቡት ጥሪ የኢትዮጵያን ታሪክና ባህል ለማወቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሐመድ አል አሩሲ ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ መሰረት የዳያስፖራ አባላቱ ከታህሳስ 20 ቀን 2016 እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም በሶስት ዙር ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ እየተሰራ ይገኛል።
ይህን አስመልከተውም መሐመድ አል አሩሲ÷ ኢትዮጵያ በዓለም አድናቆት ካገኘችባቸው ባህሎቿ፣ ትውፊቶቿና የቱሪዝም መዳረሻዎቿ ባሻገር ሰፊ የልማትና የኢንቨስትመንት እድሎች ያሏት ሀገር ናት ብለዋል።
ከዚህ አኳያ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁለተኛው ትውልድ የኢትዮጵያ ብዝኃ ባህሎችና እሴቶች እንዲሁም ያሏትን እምቅ ሀብቶች ለማወቅ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ዳያስፖራው ወደ ሀገሩ በመመለስ ያለውን ልማት እንዲመለከትና የስራው አካል እንዲሆን የሚጋብዝ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለዳያስፖራው የሚያስፈልጉ አገልግሎቶችና ምቹ ሁኔታዎች መፍጠሯን የጠቀሱት የምክር ቤት አባሉ÷ ዳያስፖራው አምባሳደር በመሆን በልማት ስራዎች፣ በመልካምና ፈታኝ ወቅቶች ከሀገሩ ጎን መቆሙን አስረድተዋል፡፡
ይህን በጎ ተግባር በማጠናከር ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ የቱሪዝም ሀብቶች በመጎብኘት ሀገራቸውን ማስተዋወቅ ከዳያስፖራው የሚጠበቅ ተግባር ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡