የመግባቢያ ስምምነቱ በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ነው – አምባሳደር ጄ ፒተር ፋም
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ነው ሲሉ በሣህል ቀጠና የቀድሞ የአሜሪካ ልዩ መልክተኛና የአትላንቲክ ካውንስል የፖለቲካ ጉዳዮች ተመራማሪ አምባሳደር ጄ ፒተር ፋም ገለጹ።
አምባሳደር ጄ ፒተር ፋም በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት÷ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ካላት የህዝብ ብዛትና የመልማት አቅም እንዲሁም ከወደብ ኪራይ ዋጋ ውድነት አንጻር በጅቡቲ ወደቦች ላይ ብቻ ጥገኛ ሆና መቀጠል እንደማትችል ከተገነዘበች ቆይታለች ብለዋል።
የመግባቢያ ስምምነቱ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለውን ነባራዊ ሁኔታዎች ያገናዘበ፣ በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
በተጨማሪም ስምምንቱ የቀጣናውን አካባቢ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ሊያሻሽል የሚችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በፈረንጆቹ በ1960ዎቹ በርካታ ሀገራት ሶማሊላንድን በነጻና ሉዓላዊት ሀገርነት እውቅና ሰጥተዋት የነበረ መሆኑን አስታውሰው ÷ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ከሶማሊያ ግዛት ጋር እንድትቀላቀል ተደርጓል ነው ያሉት።
ከዚያድ ባሬ አስተዳደር መፈራረስ በኋላ ሶማሊላንድ የራሷ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎች በማድረግ የራሷን አስተዳደር ምስረታ ከ30 ዓመታት በላይ መቆየቷንም አንስተዋል።
ከኢትዮጵያ ባሻገር ሌሎች ሀገራትም በሶማሊላንድ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ እንደሆነ መናገራቸውን ቢቢሲን ጠቅሶ የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
ለአብነትም የእንግሊዝ ኩባንያዎች ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ዱባይ ፖርትስ ኩባንያ ጋር በመሆን ቢሊየን ዶላሮችን በማውጣት በበርበራ ወደብ ልማት ላይ እየተሳተፉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ቢዘገይም ቢፈጥንም፤ ቢፈለግም ባይፈለግም ሶማሊላንድ ዓለም አቀፍ እውቅና የማግኘቷ ጉዳይ አይቀሬ ነው ሲሉም ተናግረዋል አምባሳደሩ።