ጥምቀት በኢራንቡቲ እንደወትሮው ሁሉ በድምቀት ይከበራል – መምሪያው
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተራ እና የጥምቀት በዓል በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ኢራንቡቲ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ እሴቱን ጠብቆ በሰላም እንዲከበር የዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የሰሜን ሸዋ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል፡፡
በዓሉ በስኬት እንዲከበር ለማድረግም ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከመንግሥት የጸጥታ አካላት፣ ከሐይማኖት መሪዎች፣ ከአካባቢው ነዋሪዎች እና ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ምክክር መደረጉን የመምሪያው ኃላፊ ሐይማኖት ዝቁ ተናግረዋል፡፡
በውይይቶቹ መሠረትም በዓሉን ለማክበር የሚመጡ እንግዶች የጸጥታ መደፍረስ ሥጋት እንዳይገባቸው በየደረጃው ከሚገኙ የኮማንድ ፖስት አመራሮች ጋር በቂ ውይይት መደረጉን እና መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በኢራንቡቲ የከተራና ጥምቀት በዓል በፍጹም ሰላማዊ ሁኔታ ማክበር እንደሚቻል ጠቁመው÷ በአካባቢው የመከላከያ ሠራዊት እና የመንግሥት የጸጥታ አካላት መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል እንግዶች በቂ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በተደጋጋሚ ውይይት ተደርጎ የጋራ አቋም ተይዟል ብለዋል፡፡
44 ታቦታት ወደ ባሕረ ጥምቀቱ በሚወጡባት ኢራንቡቲ የከተራና ጥምቀት በዓልን ማክበር ለሐይማኖቱ ተከታዮችም ሆነ ለሌሎች ጎብኚዎች ልዩ ስሜት እንዳለውም አመላክተዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው