በሶማሌ ክልል የተከናወነው የሙስና መከላከል ሥራ ውጤት ማምጣቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል የተከናወነው ሙስና እና ብልሹ አሰራርን የመከላከል ሥራ ውጤት ማስገኘቱን የክልሉ የሥነ -ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የኮሚሽኑ ም/ኮሚሽነር አቶ አብዲ ሽኩር እንዳሉት÷ ሙስና የክልሉን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እድገት የሚያደናቅፍ በመሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በተለይም ባለፉት 6 ወራት ሙስናን እና ብልሹ አሰራርን መከላከል እና መልካም ሥነ-ምግባር ያለው ሕብረተሰብን መፍጠር ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱን ነው የገለጹት፡፡
በዘርፉ የሚስተዋሉ ወንጀሎችን እና ሌሎች ጉድለቶችን ለመከላከል ወንጀሎችን እና ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶችን የማጋለጥና የመመርመር ሥራ መከናወኑ ተመላክቷል፡፡
ኮሚሽኑ የፀረ-ሙስና ትግሉን የመምራትና የማስተባበር ሚናውን በብቃት እንዲወጣም የማሻሻያ ሥራዎች መከናወናቸውን አቶ አብዲ ለፋና ብሮድካስቲግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
በዚህም በመንግሥት መስሪያ ቤቶች፣ በልማት ድርጅቶችና ሕዝባዊ ድርጅቶች ሙስናና ብልሹ አሠራር እንዲቀንስ እንዲሁም የአሠራር ሥርዓት ግልጽነትና ተጠያቂነት ማረጋገጥ ማስቻሉን አመልክተዋል፡፡
በክልሉ ባለፉት 6 ወራት በተከናወነ የሙስና መከላከል ሥራ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን እና ዘርፈ ብዙ ሙስናዎችን መቀነስ መቻሉንም አስረድተዋል፡፡
በሙስና መከላከል ሥራም ሊመዘበር የነበረ የተለያየ መጠን ያለው የመንግስት ሃብት እና ቦታ ማስመለስ መቻሉ ተጠቁሟል፡፡
ከሙስና እና ብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘም የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተይዘው ጉዳያቸው እየታየ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በመላኩ ገድፍ