የምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ ላይ ትኩረት ያደረገ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
ፍኖተ ካርታው ከያዛቸው ጉዳዮች መካከልም÷ ምርታማነትን መጨመር፣ የገጠር ኑሮ ማሻሻል፣ ግብርናን ከሌሎች ኢንዱስትሪዎች ጋር ማቀናጀት፣ አካባቢ ጥበቃን ማጠናከርና ከምግብ ጋር የተያያዙ የጤና ችግሮችን መግታት የሚሉት ይገኙበታል፡፡
እነዚህን ግቦች ለማሳካትም ደኅንነቱ የተጠበቀና በንጥረ ነገር የበለጸገ ምግብን ተደራሽ ማድረግ፣ የግብርና ሜካናይዜሽንን ማስፋፋት፣ የምግብ ሥርዓትን ለማሻሻል የሚረዱ ቴክሎጂዎችና ፈጠራዎች እየተተገበሩ ካሉ ተግባራት መካከል መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የጤና ሚኒስትር ደዔታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ፣ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) እና የልማት አጋሮች ተሳትፈዋል፡፡