በክልሉ በ2016/17 ከ41 ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሠራ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016/17 የመኸር ወቅት 41 ሚሊየን 548 ሺህ 712 ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያከናወነ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
ምርቱን ለማግኘትም 1 ሚሊየን 243 ሺህ 18 ሔክታር መሬት በተለያየ የሰብል ዓይት እንደሚሸፈን የቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ዳይሬክተር ፍቅሩ አቡን ገልጸዋል፡፡
የቢሮው የግብርና ግብዓት ምርት ግብይት የገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዳይሬክተር ተስፋዬ በቀለ በበኩላቸው የ2016/17 የምርት ዘመን የሚውል 203 ሺህ 510 ኩንታል ማዳበሪያ በግብርና ሚኒስቴር መፈቀዱን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ ኤንፒኤስ 113 ሺህ 20 እንዲሁም 90 ሺህ 490 ዩሪያ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ወደ ክልሉ ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ እስከ ትናንትና ድረስም ኤንፒኤስ 37 ሺህ 325 እንዲሁም 22 ሺህ 67 ዩሪያ በአጠቃላይ 59 ሺህ 392 ኩንታል ማዳበሪያ መግባቱን አረጋግጠዋል፡፡
በቀጣይም ወደ ክልሉ የገባውን ማዳበሪያ ከሥርከሥር ለአርሶ አደሩ ለማሠራጨት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
ለክልሉ የተፈቀደው ማዳበሪያ ከፍላጎቱ አንጻር በቂ ስላልሆነ አርሶ አደሩ ሌሎች አማራጮችን እንዲጠቀም እናበረታታለን ብለዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው