የሰቆጣ ቃልኪዳን ማስፋፊያ ትግበራ የሀብት ማሰባሰቢያ ዕቅድ ይፋዊ መድረክ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰቆጣ ቃልኪዳን ማስፋፊያ ትግበራ የሀብት ማሰባሰቢያ ዕቅድ ይፋዊ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በሰቆጣ ቃልኪዳን ማስፋፊያ ምዕራፍ ትግበራው በድምሩ 146 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚጠይቅ ተገልጿል።
በመድረኩ የሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮጀክት ማናጀር ዶክተር ሲሳይ ሲናሞ እንዳሉት÷ በፈረንጆቹ እስከ 2021 በነበረው የመጀመሪያው ዙር ትግበራ 59 ሺህ 717 ህፃናትን ከመቀንጨር እንዲሁም 2 ሺህ 900 በላይ ህፃናትን ከሞት ታድጓል።
ከ2021 እስከ 2030 በሚተገበረው ሁለተኛ ዙር የሰቆጣ ቃልኪዳን የማስፋፊያ ፕሮግራም የሚተገበርባቸውን ወረዳዎች በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በማስፋት በ2025 መጨረሻ 700 ለማድረስ የታቀደ ሲሆን፤ 199 ሺህ 839 ህፃናትን ከመቀንጨር እንደሚታደግ ተገልጿል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ድጉማ በበኩላቸው÷ የሰቆጣ ቃልኪዳን የደጋፊ አካላት ሀብት ማሰባሰብ ለፕሮግራሙ ስኬት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በጤናና በማህበራዊ ዘርፎች ለውጦች እያስመዘገበች መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግስት የምግብና የተመጣጠነ ምግብ ዋስትና ችግርን ለመቅረፍ በርካታ ፕሮግራሞችን ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ለዚህም የሰቆጣ ቃልኪዳን ባለፉት አስር ዓመታት ትልቅ ለውጥ እንደተመዘገበበት ገልፀው፤ መንግስት በጀት መድቦ ለትግበራው እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የግል ዘርፉ፣ የሲቪል ማህበራትና የመንግሥታቱ ድርጅት ኤጀንሲዎችን ጨምሮ አጋር አካላት ድጋፍና ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።
በፈረንጆቹ 2015 በይፋ መተግበር የጀመረው የሰቆጣ ቃልኪዳን በፈረንጆቹ 2030 ዕድሜያቸው ከ2 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት የመቀንጨር ችግርን በዘላቂነት መቅረፍ ግብ ይዞ የሚተገበር የኢትዮጵያ መንግስት ፕሮግራም ነው።
40 ወረዳዎችን በማቀፍ የተጀመረው ፕሮግራሙ በ2021 ያቀፋቸውን ወረዳዎች ወደ 240 በማሳደግ ለሀገራት ምሳሌ የሆነ ውጤታማ አፈፃፀም እንደነበረው መነሳቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡