የአፍሪካን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የትምህርት ዘርፍ የሚደረገውን መዋዕለ ንዋይ ማስፋት ይገባል – ክላቨር ጋቴቴ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በትምህርት ዘርፍ የሚደረገውን መዋዕለ ንዋይ ማስፋት እንደሚያስፍልግ በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ክላቨር ጋቴቴ ገለጹ።
በ44ኛው የአፍሪካ ሕብረት የአስፈጻሚዎች ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ላይ ክላቨር ጋቴቴ÷ አህጉራዊ የማኅበረ-ኢኮኖሚ ግቦችን ለማሳካት ትምህርት የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።
አህጉራዊ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ማረጋገጥ ካልተቻለ የአፍሪካን ሁለንተናዊ ልማት ማሳለጥ እንደሚያስቸግር አስገንዝበዋል።
በዓለም የሚከሰቱ ተለዋዋጭ ሁነቶች የተሻለ የትምህርት ሥርዓት በመዘርጋት ለቴክኖሎጂና ፈጠራ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ አመላካች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዘመናዊ ግብርና፣ ቴክኖሎጂ፣ የዲጂታል ሥርዓት፣ አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ እና ሌሎች የፈጠራ ሥራዎች ለበርካታ የኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ስኬት አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአፍሪካ ያለውን አጠቃላይ መደበኛ ትምህርት ከቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ጋር አቀናጅቶ ማስተማር ለፈጠራ ሥራ መሰረት እንደሆነም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትልምን እውን ለማድረግም በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምህንድስና እና በፈጠራ የተደገፈ የክህሎት አብዮት ያስፈልገናል ብለዋል።
የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማስፋት ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ብቁ የሰው ሃይል ማፍራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
የሕብረቱ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ “ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ ማስተማር” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ይገኛል።