ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ሁሉም የበኩሉን ሃላፊነት ሊወጣ ይገባል – አቶ እንዳሻው ጣሰው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ሁሉም የበኩሉን ሃላፊነት ሊወጣ ይገባል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳደር እንዳሻው ጣሰው ገለጹ፡፡
በጋምቤላ ክልል “ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ሃሳብ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ ማጠቃለያ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ከመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያዎች ተሰጥቷል፡፡
አቶ እንዳሻው ጣሰው ሰላምና ደህንነትን በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ ሰላም በሕግ ማስከበር የሚረጋገጥ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
የጋምቤላ ክልል የሰላምና ፀጥታ ችግር በዋናነት በአመራሩ መካከል ባለ መናናቅና መገፋፋት እንዲሁም የማህበራዊ አንቂ ነን በሚሉ ሃላፊነት በጎደላቸው ግለሰቦች የመጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም አመራሩ በመቀራረብ ፣ በመነጋገርና በመተጋገዝ ቢሰራ ችግሩ ይቀረፋል ያሉ ሲሆን÷ ሃላፊነት በጎደላቸው ማህበራዊ አንቂዎች ላይም እርምጃ በመውሰድ ችግሩን ለማቃለል መስራት ይጠበቃል ብለዋል።
የኑሮ ውድነቱን አስመልክተው በሰጡት ምላሽም አሁን ላይ ምርታማነትን ማሳደግና መጨመር እንዲሁም የንግድ ሰንሰለቱን መቀነስ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ገበያዎችን ማስፋትና የገበያ ስርዓቱን በትክክለኛው መንገድ መምራት እንዲሁም ኬላዎችን መቀነስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በጋምቤላ ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ ውይይት ላይ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ፣ የኑሮ ውድነት ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች እንዲሁም ትውልድ ግንባታ ላይ ያተኮሩ ሀሳቦች ቀርበዋል።
በተለይም በጋምቤላ ከተማ ያለው የፀጥታ ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን ያነሱት ነዋሪዎቹ÷ አሁን ላይ ዝርፊያና ቅሚያ በስፋት መንሰራፋቱን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ግለሰቦች የፈጠሩትን የወንጀል ተግባር የቡድንና የብሔር በማስመሰል ብሔር ብሔረሰቦችን ለማናቆር የሚሰራው ስራ መቀረፍ እንደሚገባው ተናግረዋል።
ከኑሮ ውድነት ጋር በተገናኘም ነዋሪው በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈተነ እንደሚገኝ ነው የተጠቆመው፡፡
የሀረሪ ክልል ምክር ቤት ም/ አፈጉባኤ አቶ አሪፍ መሃመድ በበኩላቸው÷ ከጤናና ከትምህርት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ጋር የተገናኙ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች በክልሉ አቅም እንደሚፈቱ ጠቅሰዋል፡፡
የፌደራል መንግስቱን የሚመለከቱ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ደግሞ ባለድርሻዎች ወስደው እንደሚሰሩባቸው ተናግረዋል።
በዓለምሰገድ አሳዬ
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!