Fana: At a Speed of Life!

ሕዝባዊ ውይይቶች ሀገራዊ ፈተናዎችን ለመፍታት ሚናቸው ከፍተኛ ነው – ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በየከተሞች የሚደረጉ ውይይቶች ሀገራዊና ክልላዊ ፈተናዎችን ለመፍታት ዓይነተኛ ሚና አላቸው ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለፁ።

“ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ህዝባዊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ ከተሳታፊዎች የልማት፣ የሰላም፣ የኑሮ ውድነት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር እና ከስራ አጥነት ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ ችግሮች ተነስተዋል።

በተለይም ክልሉ የአርብቶ አደርና ከፊል አርሶ አደር እንደመሆኑ ከዚህ ጋር ተያይዞ የወተትና የስጋ ተዋፅዖዎችን ለህብረተሰቡ በስፋት ማቅረብ እንዲቻል ለማድረግ የብድርና ሙያዊ ድጋፎች እንዲደረጉ ተጠይቋል።

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ግጭት ጉዳት የደረሰባቸው የመሰረተ ልማት አገልግሎቶች አስፈላጊው ጥገና እንዲደረግላቸውም በመድረኩ ተነስቷል።

ክልሉ በማዕድን ሀብት እጅግ የበለፀገ በመሆኑ የማሽነሪዎች ድጋፍና የክህሎት ስልጠና ተሰጥቷቸው በማህበር በመሆን እንዲያለሙ የሚያስችል እድል እንዲመቻችላቸውም ጥያቄያ አቅርበዋል።

የአፋር ክልልን ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኘው ድልድይ ረጅም ዓመታት በማስቆጠሩ አስፈላጊውን እድሳት እንዲደረግለትም ተሳታፊዎቹ አንስተዋል።

በተለይም በለውጡ ማግስት ክልሉ የልማት ተጠቃሚ እንደሆነና በአሁኑ ሰዓት የሩዝ፣ የስንዴና የጤፍ ምርቶችን በማምረት ረገድ ሰፊ ስራ እንደተሰራ ነዋሪዎቹ ገልፀዋል።

መድረኩን የመሩት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች÷ የተነሱ ጥያቄዎች አግባብነት እንዳላቸው ገልጸው፤ መንግስት ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከባንክ፣ ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት፣ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ እንደሆነም አመልክተዋል።

በታሪኩ ወ/ሰንበት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.