በምእራብ ኦሮሚያ ዞኖችና የተለያዩ አካባቢዎች በግድያና ዘረፋ ወንጀል የተጠረጠሩ 48 ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በምእራብ ኦሮሚያ ዞኖችና የተለያዩ አካባቢዎች በግድያና ዘረፋ ወንጀል ላይ ተሰማርተው የነበሩ 48 ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል ክትትል ዘርፍ አዛዥ ግርማ ገላን በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፥ “አባ ቶርቤ” በሚል ስም ተደራጅተው የሰዎችን ህይወት ሲያጠፉ የነበሩ ግለሰቦብ በተደረገው ፍተሻና ክትትል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል።
በቄለም ወለጋ ዞን፣ በነቀምቴ እና በቡራዩ ከተሞች ሲፈፀሙ የነበሩ ጥፋቶችን በተመለከተ በጉዳዩ ላይ ትእዛዝ ሲሰጡ የነበሩ ሀይሎችን እና ጥፋቱን ሲፈፅሙ የነበሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለ አስታውቅዋል።
ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘም መንግስት ሙሉ ማስረጃ እንዳለውም ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ገላን ተናግረዋል።
እነዚህ የጥፋት ሀይሎች 4 የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ወንጀሎችን ሲፈጽሙ እንደነበረም መግለፃቸውንም የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
ስልቶቹም በጫካ ውስጥ ታጥቆ መንቀሳቀስ፣ “አባ ቶርቤ” በሚል የተደራጀ ሀይል የመንግስት የስራ ሃላፊዎችንና ባለሀብቶችን ህይወት ማጥፋት፣ በአክቲቪስት ስም የተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ድረ ገፆችን በመጠቀም ህዝብ ውስጥ ውዥንብር መፍጠር እንዲሁም ምርጫ ላይ ሀይል ለመጠቀም አቅደው እንደነበረ ተደርሶበታል ብለዋል።
ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ገላን አክለውም በኦነግ ሸኔ ስም በምእራብ ኦሮሚያ ቄለም ወለጋ ውስጥ 212 ሰዎች ካይ ጉዳት መድረሱን እና በሰዮ ከተማ ውስጥ ደግሞ 114 ሰዎች በዚሁ ሀይል ህይወታቸው ማለፉንም አስታውቀዋል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።