የ2ኛው የመካከለኛ ዘመን የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድን ለማዳበር ያለመ ግምገማ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፕላንና ልማት ሚኒስቴር በረቂቅ ደረጃ የተዘጋጀውን የሁለተኛው የመካከለኛ ዘመን (የ2016-2018) የልማት እና ኢንቨስትመንት ዕቅድን ይበልጥ ለማዳበር ያለመ ግምገማ አካሄደ፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) የግምገማ መድረኩ አስፈላጊነት ግብዓቶችን ማሰባሰብ መሆኑን ጠቁመው÷ በዕቅዱ የተካተቱ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርምን ጨምሮ የታቀዱ የሪፎርም ሥራዎች እና ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች ላይ በመምከር የመጨረሻውን ረቂቅ ማቅረብ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴዔታ ነመራ ገበየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው የቀረበው የሁለተኛው የመካከለኛ ዘመን የልማት እና ኢንቨስትመንት ዕቅድ ብዙ ነገሮችን የሚነካ በመሆኑ ወደ ተግባር ከመሄዱ በፊት ተቋማት ሊታዩ ይገባቸዋል የሚሉትን ሐሳብ በፅሑፍ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል፡፡
በሌላ በኩል ዘላቂ የማክሮኢኮኖሚ አሥተዳደርና ዕድገት የፖሊሲ አቅጣጫ ላይ ገቢዎች ሚኒስቴር፣ ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ብሔራዊ ባንክ፣ ፕላንና ልማት ሚኒስቴር እና ተጠሪዎቻቸው እንዲሁም የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባላስልጣን ውይይት አድርገዋል፤ የተቋማቱ የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸምም ቀርቦ ተመክሮበታል፡፡
በውይይቱም በመካከለኛ ዘመን የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅዱ አሁን ያለውን የሀብት አመዳደብ ከውጤት ጋር ለማስተሳስር፣ የሁለተኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚክ ሪፎርም ከመካከለኛ ዘመን ዕቅዱ ጋር የተካተተበት አግባብ አበረታች ነው ተብሏል፡፡
የሚቀሩ የተለዩ የሪፎርም ሥራዎች መቼ መጠናቀቅ እንዳለባቸው፣ ያልተሞሉ ኢላማዎች ጭምር ተስተካክለው እንዲቀርቡም የየተቋማቱ ኃላፊዎች ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
የኢንቨስትመንት ዕቅዱን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ከሀገሪቱን የበጀት አቅም ጋር የተናበበ እንደሚሆን በውይይቱ የተነሳ ሲሆን÷ ይህንም ለዘርፎች ከሚሰጠው የበጀት ጣሪያ ጋር የተቆራኘ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
ከመካካለኛ ዘመን ዕቅዱ ጋር በተያያዘ የተቀረፁ ፕሮግራሞች ሀገራዊ ስትራቴጂክ ግቦችን መሰረት አድርገው መቀረጻቸው የተገለጸ ሲሆን÷ ይህንም ከዚህ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ከስምምነት ተደርሷል።