Fana: At a Speed of Life!

75ኛው የጉጂ ኦሮሞ አባ ገዳ ስልጣን ርክክብ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 75ኛው የጉጂ ኦሮሞ አባ ገዳ ስልጣን ርክክብ ተካሂዷል፡፡
 
በዚህም መሰረት አባገዳ ጂሎ ማንዶ ስልጣናቸውን ለአባ ገዳ ጃርሶ ዱጎ አስረክበዋል፡፡
 
ከቀናት በፊት በሜኤ ቦኮ የተሰባሰቡ አባ ገዳዎችና በተለያዩ የገዳ ስርአት እርከን ውስጥ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የተለያዩ ስርአቶችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል።
 
በየስምንት አመቱ በሚካሄደው የስልጣን ርክክብ መሰረት ዛሬ ከገዳ ሀርሙፋ ወደ ገዳ ሮበሌ ሽግግር ተደርጓል።
 
በአርዳ ጂላ ሜኤ ቦኮ አባገዳዎች የገዳ ስርአት ለሰው ልጅ፣ ለእንስሳት እና ለተፈጥሮ የሰጠው መብት አፅንኦት የሚሰጥበት የተለያዩ አዋጆችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል።
 
ለአብነትም÷ ሰላም እና እርቅ ማስፈንን በተመለከተ ከስርዓቱ ማፈንገጥ ተቀባይነት እንደሌለው አውጀዋል።
 
ባህልን መጠበቅና መከተል ግዴታ መሆኑን፣ ስለ ጋብቻ ስርአት እና የተከለከሉ ተግባራትን በተለይም በጋብቻ በሴት ቤተሰብ የሚጠየቅ ከፍተኛ ገንዘብ ተገቢ አለመሆኑንና ሌሎች ጉዳዮች በተመለከተም አውጀዋል።
 
ስለካሳ ሁኔታ:- የተበዳይ እና ካሳ ሰጪ ግዴታዎች፣ ስለ ተፈጥሮ ጥበቃ ማለትም (የመሬት፣ የወንዞች፣ ሀይቆች፣ መንገድ እና መሰል ጉዳዮች)፣ ስለ ደን እና እንስሳት ጥበቃ (ደን መጨፍጨፍ እና እንስሳትን መጠለያ ማሳጣት፣ ዝርያን ማመናመን እንደማይፈቀድ) አውጀዋል።
 
ስለ አለባበስ ስርአት በአደጋ ሲከሰት እና ወረርሽኝ ሲኖር ስለማሳወቅና ሌሎች ተያያዝ ጉዳዮች ላይም አፅንኦት የሚሰጡ ውሳኔዎችን አውጀዋል።
 
በተለያዩ ምክንያቶች የተቸገረን ሰው መርዳት፣ እርዳታ መስጠት ስርአቱ እንደሚያዝ አውጀዋል።
 
በየአካባቢው ያሉ አርዳ ጂላዎች ማለትም እንደ ሜኤ ቦኮ ያሉ የስልጣን ርክክብ ማድረጊያ ቦታዎች እንዲከበሩ እና መጠበቅም እንዳለባቸው አውጀዋል።
 
ከዚህም ባሻገር የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ስርአቱ የሰጣቸው መብትና ግዴታ ትውልድ እንዲያስቀጥለው እንዳስገነዘቡ የምእራብ ጉጂ ዞን ኮሙኒኬሽን ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ገመቹ ገብረማርያም ገልጸዋል።
 
በስልጣን ርክክብ ስነስርአቱ 74ኛው የጉጂ አባ ገዳ ጂሎ ማንዶ ስልጣን በማስረከብ በሀዩ ገዳነት (በአማካሪነት) የሚያገለግሉ ይሆናል።
 
በማርታ ጌታቸው
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.