የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የነፃነት፣ የእኩልነትና የአልገዛም ባይነት አርማ ነው- አቶ አወል አርባ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ 128ኛውን የዓድዋ ድል በዓል አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም ÷ ዓድዋ ለመላ ኢትዮጵያን እና ወዳጆቸ የነፃነት፣ የእኩልነትና የአልገዛም ባይነት አርማ ከመሆኑ በሻገር ለመላው ጭቁን ሕዝቦቸ የድል ችቦ የለኮሰ ድል ነው ብለዋል፡፡
ቅኝ ግዛት ከዓለማችን እንዲወገድ ፈር ቀዳጅ የሆነው የዓድዋ ድል ቀንን አስበን ስንውል እኒያ አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍስሰው መስዋዕትነት ከፍለው ሀገር ላቆሙ አርበኞቻችን ክብርና ሞገስ በመስጠት ሊሆን ይገባል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
አባት አርበኞች የውስጥ ልዩነቶቻቸውን በመቻቻል ከሁሉም የኢትዮጵያ ማዕዘናት በአንድነት በመነሳት ወራሪ ሃይልን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት የዓለማችንን የተዛባ ትርክት “ጥቁር የቆዳ ቀለም ያለው የሰው ዘር የበታቸ ነው” የሚለውን ጥቁርም ሆነ ነጭ ሁሉም የሰው ዘር እኩል መሆኑን በማስመስከር ደማቅ የታሪክ አሻራ አሳርፈዋል ነው ያሉት።
የአፋር ህዝብም ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድም እህቶቹ ጋር ለሀገሩ ተዋድቋል፤ ደማቅ አሻራንም ፅፏል፤ለዘመናት የሰሜን ምስራቅ በረኛ በመሆን ኢትዮጵያን ለመውረር የመጡ የተለያዩ ሃይሎችን አሳፍሮ፣ ውርደትና ሽንፈትን አከናንቦ መልሷል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ጉዳይም አሁንም ድረስ የአፋር ህዝብ ጋሻና መከታ ሆኖ የጀግንነትና የአርበኝነት ተምሳሌት ሆኗል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው።
የዛሬው ትውልድ እንደትናንቱ ትውልድ ሁሉ የራሱን ታሪክና አሻራ በማስቀመጥ የትውልድ ቅብብሎሽ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ሁሌም ለሀገሩ ቅድሚያ የሚሰጥ፣ በሀገር ጥቅም ጉዳይ ፈፅሞ የማይደራደር፣ ለሀገሩ ሁሌም ዘብ የሚቆም ከታሪከ ተወቃሽነት ነፃ መሆን ይኖርብናል ብለዋል፡፡
የዓድዋ ድል በዓልን ስናከብርም ነጠላ፣ አግላይ እና ከፋፋይ ትርክቶችን ወደ ኋላ በመተው፤ ገዢ፣ አሰባሳቢና ህብረ ብሄራዊነታችን የሚያጠናክሩ ትርክቶችን በማስፋት መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡