በክልሉ 43 በመቶ የሚደርሰውን በረሃማነት ጠባይ ያለው መሬት ማልማት መቻሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል እስከ 43 በመቶ የሚደርሰውን በረሃማነት ጠባይ ያለው መሬት በሳይንሳዊ ጥናት ተመርኩዞ ማልማት መቻሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሺመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
አካባቢው በተደጋጋሚ ሲያስተናግድ የኖረው የዝናብ እጥረትና ድርቅ፣ በክልሉና በሀገር ላይም ከፍተኛ ፈተና ሆኖ መዝለቁን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
ሆኖም ከለውጡ በኋላ ለዘመናት ያለመፍትሄ የኖረውን የማህበረሰብ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት ሳይንሳዊ ጥናት አስፈላጊ መሆኑን አቋም ይዞ መነሳቱን አመላክተዋል፡፡
ይህንንም ተከትሎ በተካሄደ ጥናት፣ አካባቢው ከፍተኛ የሆነ የመሬት፣ የውሃ፣ የእንስሳት ሃብትና የመልማት አቅም እንዳሉ መለየት መቻሉን አንስተዋል።
በዚህም መንግሥት ክፍት የግጦሽ መሬት ማልማት፣ የመሠረተ ልማት ግንባታ በብዛት፣ በጥራትና በፍጥነት ማስፋፋት እንዲሁም የማህበረሰቡን ኑሮና ህይወት ማሻሻል የሚሉ ሦስት የትኩረት አቅጣጫዎች ይዞ ወደ ስራ መግባቱን አቶ ሽመልስ ተናግረዋል፡፡
የአካባቢውን የአየር ንብረት ተፅእኖ በመቀነስና ዘላቂ የመሬት አስተዳደር በመዘርጋት ግብርናን የማስፋትና ምርታማነትን የማሳደግ ሰፊ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በዚህ ረገድ የውኃ ማጠራቀምና ማሰራጨት ስራዎች ዋነኞቹ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
በክልሉ እየተተገበሩ ካሉት 73 የግድብ ፕሮጀክቶች ግማሽ ያህሉ በአርብቶ አደር አካባቢዎች እንደሚገኙና በአጭር ጊዜ ውስጥም ከፍተኛ ውጤት እያስገኙ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት ብቻ በ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር 12 ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ 2 ሺህ 899 ሄክታር መሬት ወደ ግብርና ልማት ማስገባት እንደተቻለና 16 ሺህ 910 አባወራዎችን ተጠቃሚ እንዳደረገ ተናግረዋል።
ዘንድሮ ደግሞ በጀቱን በእጥፍ በማሳደግ 19 የሚሆኑ ፕሮጀክቶች እንደተጀመሩና ከዚህም ውስጥ ሁለቱ መጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል።
በተጨማሪ 7 ሺህ 410 ሄክታር መሬት ወደ ግብርና ልማት የገባ ሲሆን÷ 15 ሺህ 791 አባወራዎች ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውንም አንስተዋል።
የክልሉ መንግስት ለግብርና ግብአቶችና ማስፋፊያ የሚውሉ የብድር አገልግሎቶችን ለማመቻቸትና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ሰፊ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!