በድላችን ሐውልት ከተቀረጸላቸው የካራማራ ጀግኖች መካከል…
አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባ በሚገኘው ድላችን ሐውልት ከተቀረጸላቸው የካራማራ ዘማቾች መካከል አምሳ አለቃ መዓዛ ታደሰ እና አቶ በቀለ ገመቹን በወፍ በረር እናስቃኛችሁ፡፡
አምሳ አለቃ መአዛ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ የቀድሞ የሠራዊቱ አባል መሆናቸውን አስታውሰው በወቅቱም በማዕከላዊ ዕዝ የቅስቀሳ እና ፖለቲካ ሥራ በማከናወን የሶማሊያን ጦር መታገላቸውን አንስተዋል፡፡
በነበራቸው አስተዋጽኦም ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው ኢትዮ ኩባ ወዳጅነት ፓርክ ውስጥ ባለው ድላችን ሐውልት ላይ ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ከያዘው አቶ በቀለ ገመቹ በስተግራ በኩል ተቀምጠዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም 46ኛውን የካራማራ ድል ሐውልቱ በሚገኝበት ሥፍራ ተገኝተው ያከበሩ ሲሆን÷ በቦታው ተገኝተው ድሉን ሲያከብሩም ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ለሀገሬ የሠራሁት በማይደበዝዝ የታሪክ ሐውልት ላይ መቀመጡ አስደስቶኛል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ሌላኛው በድላችን ሐውልት ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ይዘው ሐውልት የተቀረጸላቸው ጀግና በሙያቸው ኤሌክትሪሺያን የሆኑት የካራማራው ዘማች አቶ በቀለ ገመቹ በቅጽል ስማቸው አሚኮ ናቸው፡፡
በ1969 ዓ.ም በዚያድ ባሬ የሚመራው የሶማሊያ አገዛዝ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት መዝመታቸውን አንስተዋል፡፡
ከመዝመታቸው ባሻገር የኤሌክትሪክ ባለሙያ በመሆናቸው “በራ በራ የድል ጮራ” የተሰኘውን ዓርማ በመቅረጽ በ14ቱ ክፍለ ሀገሮች እንዲበራ ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል፡፡
በዚህም ከወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም እና ከኩባው ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮ ሽልማት እንደተበረከተላቸው ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
በድላችን ሐውልት ላይም ክላሽንኮቭ መሳሪያ ይዘው ሐውልት ተቀርጾላቸዋል።
ሐውልቱ እንዲቀረጽ የተደረገበት ፎቶግራፍ በያኔው ሦስተኛው አንበሳው ክፍለ ጦር በኋለኛው ምሥራቅ ዕዝ በር ላይ ክላሽንኮቭ ይዘው የተነሱት ፎቶ ግራፍ መሆኑን አስታውሰው÷ በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡
ከእርሳቸው ጎንም መንበረ የምትባል ሌላ ዘማችና መትረየስ ተኳሽ ሴት ባደረገችው አስተዋፅኦና በደረሰባት የአካል ጉዳት ሐውልት እንደተቀረጸላት ጠቁመዋል፡፡
የካራማራ ድል በርካታ ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ከፍለውበት የተገኘና ሀገርን ያስከበረ ነውም ይላሉ፡፡
ሶማሊያን ለ21 ዓመታት ያሥተዳደሩት ዚያድ ባሬ ‘ታላቋን የሶማሊያ ሪፐብሊክ ለመመስረት’ በሚል “ድንበራችን እስከ አዋሽ ይደርሳል” እያሉ በመዛት የጦርነት ነጋሪት መጎሰማቸው ይታወሳል፡፡
ይህን እውን ለማድረግም በ1969 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ግልጽ ወረራ ፈጸሙ።
የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጦር የእብሪተኛውን የዚያድ ባሬ ጦር ካራ ማራ ላይ ድል በማድረጉ፤ የኢትዮጵያ አሸናፊነት በአደባባይ ታወጀ።
ድሉ በየዓመቱ የካቲት 26 ቀን የሚታሰብ ሲሆን ዘንድሮም 46ኛ ዓመቱ ታስቧል፡፡
በማርታ ጌታቸው