መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት በውጪ ሀገራት የነበሩ 180 ሺህ ዜጎች ወደ ሀገራቸው ተመለሱ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከልና የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ በመቀሌ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
መድረኩ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከልና ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ህብረት ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ ሁሪያ አሊ÷መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ከሀገር ወጥተው የነበሩ 180 ሺህ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል።
መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት ተጎጂ የሆኑ ተመላሾችን መልሶ ማቋቋምና ለዳግም ስደት እንዳይጋለጡ የማድረግ ሥራ ትኩረት የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የማህበራዊ ጉዳይና የመልሶ ማቋቋም ክላስተር ሃላፊ ጄነራል ተክላይ አሸብር በበኩላቸው÷በአሁኑ ወቅት ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና የወጣቶች ፍልሰት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አንስተዋል፡፡
በሱዳንና በሊቢያ አድርገው ወደ አውሮፓ እንዲሁም የጅቡቲንና የየመንን በረሃዎችና ባህር በማቋረጥ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያና ሌሎች የዓረብ ሀገራት በሚያደርጉት ጉዞ ዜጎች ለችግር እየተጋለጡ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
መድረኩ ችግሩን ለመፍታት እንደሚያግዝ መገለጹን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡